“ብዙዎች በዱባይ ስምምነት አይደረስም ቢሉም አሳክተነዋል” - አልጀበር
ኤምሬትስ የተሳካ ጉባኤ በመዘጋጀቷ እንደምትኮራም የኮፕ28 ፕሬዝዳንት በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ተናግረዋል
ሀገራት በዱባይ የገቡትን ቃል በመፈጸም ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩም ጠይቀዋል
የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ታሪካዊ ነው የተባለለት የ”ኤምሬትስ ስምምነት” ሲፈረም ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ስኬታማ ጉባኤ ማስተናገዷን ተናግረዋል።
“ብዙዎች በኮፕ28 ስምምነት አይደረስ ቢሉም፤ በጉባኤው መክፈቻ እንዳልኳችሁ የዱባዩ ጉባኤ ከቀደምቶቹ የተለየ ነው፤ ታሪካዊ ስምምነት ደርሰናል” ነው ያሉት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር።
ሀገራቸው የተሳካ ጉባኤ በማዘጋጀቷ ኩራት እንደሚሰማቸው በመግለጽም ሀገራት የተራራቀ አቋማቸውን አቀራርበው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው አመስግነዋል።
የአለም ሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይበልጥ በሳይንሳዊ መረጃ የተመሰረተ መፍትሄዎችን አስቀምጠናልም ነው ያሉት።
ጉባኤው ከመንግስትና ከግል ሴክተሮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከወጣቶችና ከሲቪል ማህበራት ተወካዮች ያላሳተፈው የህብረተሰብ ክፍል የለም” ያሉት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት፥ የጉባኤው አካታችነት የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲቀርቡ ማድረጉን አብራርተዋል።
ጉባኤው የአየር ንብረት የሚያደርሰውን ጉዳትና ኢሳራ ለሚያካክሱ ስራዎች የሚውል ፈንድ አቋቁሟል፤ ከ85 ቢሊየን ዶላር ለመለገስም ቃል ተገብቶበታል ነው ያሉት።
“አልቴራ” የተሰኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ፈንድም ሌላኛው የኮፕ28 ስኬት መሆኑንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
ከ52 በላይ የነዳጅና ጋዝ ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቴንና ሌሎች ጋዞችን ብክለት ለመቀነስ የደረሱት ስምምነት የዱባዩ ጉባኤ ስኬት ማሳያ አድርገው አቅርበውታል።
በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች “ንጹህ፣ የበለጸገችና ፍትሃዊ የሆነች ምድርን” እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆናቸውን በመጥቀስም ሀገራት በዱባይ የገቡትን ቃል ተፈጻሚ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።