የኮፕ28 ፕሬዝዳንት በኬንያ ከብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂን ያስተዋወቁ ወጣቶችን አነጋገሩ
ዶክተር ሱልጣን አልጀበር የ“ኤም ኮፓ” እና “ማዚ ሞቢሊቲ” ኩባንያዎች የፈጠራ ውጤቶችንም ጎብኝተዋል
ኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎችን የሚያቀርበው “ኤም ኮፓ” የ2015ቱን የዛይድ የዘላቂነት ሽልማትን ወስዷል
በአፍሪካ የኢነርጂ ፎረም ለመሳተፍ ኬንያ ናይሮቢ የሚገኙት የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ኬንያውያን ስራ ፈጣሪዎችን ጎብኝተዋል።
ዶክተር ሱልጣን “ኤም ኮፓ” እና “ማዚ ሞቢሊቲ” የተሰኙ በህልመኛ ወጣቶች የተቋቋሙ ኩባንያዎችን ነው የጎበኙት።
ኩባንያዎቹ ከብክለት የጸዳ፣ ዘላቂ እና ሁሉንም አካታች የሆነ ስራቸው እያስገኘ ያለውን ውጤትም ለኮፕ28 ፕሬዝዳንቱ ገለጻ አድርገዋል።
በፈረንጆቹ 2012 የተቋቋመው “ኤም ኮፓ” ከባንክ ብድር መውሰድ ለማይችሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኬንያውያን ብድር የሚያቀርብ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ በርካታ ሞተር ሳይክሎችን ማስማራቱና ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠሩም ተገልጿል።
“ኤም ኮፓ” በያዘው ከብክለት የጸዳ ዘላቂ ፕሮጀክት የ2015ቱን የዛይድ የዘላቂነት ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።
“ማዚ ሞቢሊቲ”ም በኬንያ ብሎም በመላው አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ለማቅረብ እየተንቀሳቀስ የሚገኝ ተቋም ነው።
የ2023 የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሱልጣን አልጀበርም የሁለቱን ኩባንያዎች የስራ እንቅስቃሴ ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቀንሱ የፈጠራ ስራዎች በፋይናንስ ሊደገፉ እንደሚገባም በዚሁ ወቅት አንስተዋል።
የኮፕ28 አዘጋጇ ሀገር አረብ ኤምሬትስ 2023ን የዘላቂነት አመት ብላ ማወጇ ይታወሳል።
በዛይድ የዘላቂነት ሽልማት በኩልም አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአለም የአየር ንብረት ለውጥ የሚገቱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አወዳድራ እየሸለመች ነው።