የአል ጀበር የኮፕ 28 ፕሬዝዳንትነት ለአፍሪካ ምን ፋይዳ አለው?
የአፍሪካ የኢነርጂ ምክርቤት ዳይሬክተር ኒጄ አዩክ፥ ሱልጣን አል ጀበር በአፍሪካ በታዳሽ ሃይል ልማት እያካሄዱት ያለውን አቢዮት ሰፋ ያለ ትንታኔ ጽፈውበታል
ዶክተር አል ጀበር ኢትዮጵያን ጨምሮ በ40 ሀገራት በታዳሽ ሃይል ላይ የሚሰራ ማስዳር የተሰኘ ድርጅትን ይመራሉ
ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ትክክለኛው የኮፕ 28 መሪ ናቸው አሉ የአፍሪካ የኢነርጂ ምክርቤት ዳይሬክተር ኒጄ አዩክ።
በአፍሪካ የኢነርጂ ሃብትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጽሃፍትን የጻፉት አዩክ፥ ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ጀምሮ በአንዳንድ ወገኖች የሚነሳውን ወቀሳ ውድቅ ያደረገ ሰፊ ትንታኔያቸውን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኒውስ ድረገጽ ላይ አስፍረዋል።
አል ጀበር የኤምሬትስ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሆነው ሳለ እንዴት የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ሆነው ይመረጣሉ የሚለው መከራከሪያም አል ጀበር የሚያከናውኗቸውን የታዳሽ ሃይል ልማት ስራዎች ካለመረዳት የመነጩ መሆናቸውን ያብራራሉ።
የአየር ብክለትን እያስከተለ ከሚገኘው የነዳጅ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ታዳሽ ሃይል ሽግግር ለማድረግ ጊዜ እንደሚፈልግና አውሮፓ በአሁኑ ወቅት የገጠመውን የሃይል እጥረት በመመልከት መረዳት ይቻላል ይላሉ።
ዶክተር አል ጀበር ሽግግሩ ጊዜ እንደሚወስድ ከመረዳታቸው ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚካሄዱ ስራዎች የሃይል አቅርቦት ችግር እንዳያመጡና እድገትን ወደኋላ እንዳይጎትቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲወተውቱ መቆየታቸውንም አዩክ ያወሳሉ።
አል ጀበር በታዳሽ ሃይል ልማት የሚያከናውኗቸው ፈር ቀዳጅ ስራዎችም የሚያስወድሳቸው መሆናቸውን ነው በጽሁፋቸው ያሰፈሩት።
ማስዳር - የታዳሽ ሃይል ልማት ኩባንያ
ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ከ40 በላይ ሀገራት በታዳሽ ሃይል ልማት የተሰማራውንና ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸውን ፕሮጀክቶች የሚያስተዳድረው ማስዳር ኩባንያ ይመራሉ።
ኩባንያው በኢትዮጵያ ከጸሃይ 500 ሜጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለመጀመር በጥር ወር 2023 ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
በዛምቢያም በተመሳሳይ የሶላር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጀምሯል።
ማስዳር ከአራት የሆላንድ ኩባንያዎች ጋርም በአረንጓዴ ሃይድሮጅን አቅርቦት ዙሪያ በቅርቡ ስምምነት መፈራረሙን አውስተዋል የአፍሪካ የኢነርጂ ምክርቤት ዳይሬክተሩ ኒጄ አዩክ።
አረብ ኤምሬትስ እስከ 2030 የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እና ተያያዥ ስራዎች 15 ቢሊየን ዶላር መድባ እየሰራች ነው፤ ይህንንም በዋናነት የሚመሩት ዶክተር ሱልጣንን አል ጀበር ናቸው የሚሉት አዩክ፥ አል ጀበር የኮፕ 28 ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አፍሪካ ባሉ አህጉራት ላይም የሚመሩት ኩባንያ ማስዳር በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ የሚያከናውነው ስራ የኢነርጂ ሽግግሩ ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው።
የአፍሪካን የመልማት ፍላጎት ለመመለስ የሃይል ርሃቧን ማስታገስ እንደሚገባም በማንሳት፥ ማስዳር የታዳሽ ሃይል ልማት ፕሮጀክቶቹን እንዲያስፋፋ ነው የጠየቁት።
ኤምሬትስ በህዳር ወር በዱባይ በምታስተናግደው አለምአቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤም ሱልጣን አል ጀበር ለአፍሪካ የሚበጁ ሃሳቦችን ወደ መድረክ ይዘው እንደሚቀርቡ እምነታቸውን ገልጸዋል።