ፖለቲካ
አረብ ኤምሬትስ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉባኤ ለማሰናዳት ትፈልጋለች- የ"ኮፕ 28" ቢሮ ዋና ዳይሬክተር
ሀገሪቱ የነዳጅ ኢንዱስትሪው በንግግሮች ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ ቁልፍ ነው ብላለች
በዱባይ የሚደረገው ኮፕ 28 የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመቀነስ አመርቂ ውጤት የሚመጣበት እንዲሆን ተወጥኗል
አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ እውነተኛ ውጤቶችን የሚያመጣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) ለማዘጋጀት ፍላጎት አላት።
ይህን ያሉት የኮፕ 28 ዋና ዳይሬክተር እና ልዩ ተወካይ አምባሳደር ማጂድ አል ሱዋይዲ ናቸው።
አምባሳደሩ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የፊታችን ህዳርና ታህሳስ ላይ የምታስተናግደው የአየር ንብረት ጉባኤ የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት የሚመጣበት እንዲሆን ትፈልጋለች።
ይህን ለማድረግ ግን የቅሪተ አካል ነዳጅ አምራች ተወካዮች በንግግሮች ላይ እንዲገኙ እንደሚፈልግ አስረድተዋል።
ፍሬውን እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ለመወያየት የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉባኤውን ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 (በፈረንጆች) በዱባይ ታስተናግዳለች።
"የመሪዎች መመሪያ ለእኔ፣ ለቡድናችን እና ለፕሬዝዳንታችን ግልጽ ነው። ሌላ ኮፕ ማካሄድ አይፈልጉም። ሁላችንም የፓሪስን ግቦች ለማሳካት መንገድ ላይ እንዳልሆንን እናውቃለን። ጨዋታን የሚቀይር እውነተኛ ውጤት ከኮፕ ይፈልጋሉ" ሲሉ አል ሱዋይዲ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ይህንን እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ሁሉም በጠረጴዛው ላይ እንዲወያይ እንፈልጋለን ሲሉም አክለዋል።
"ዘይትና ነዳጅ ሊኖረን ይገባል። ኢንዱስትሪውን እንፈልጋለን። አቪየሽን እንፈልጋለን። የመርከብ ትራንስፖርት እንፈልጋለን። የልቀት ቅነሳው አስቸጋሪ የሆነባቸው ዘርፎች ሁሉ ያስፈልጉናል። ማንም ይሁኑ ማን የሚችሉትን ሁሉ እንፈልጋለን" በማለት አል ሱዋይዲ አክለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም የነዳጅ ኢንዱስትሪው የአየር ንብረት ለውጥ ንግግሮች ላይ ጫና ፈጥሯል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።
"የዘርፉ አቋም ሙሉ ለሙሉ መቀየሩ ምንም ጥርጥር የለውም" ብለዋል።
"ከእኛ ጋር ንቁ ውይይት እያደረጉ ነው" በማለትም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ በሆኑ ሀገራት ነዳጆችን ማልማት የማቆም በሚል የቀረበው ጉዳይ የተጠየቁት አል ሱዋይዲ የፕሬዝዳንቱ ንግግሮች ምንም እንቅፋት እንደማይሆኑ ተናግረዋል።
አክለውም "ማንኛውም አይነት ውይይት በደስታ እንቀበላለን።ነገር ግን ውይይቱ ምን እንደሆነ እና የት እንደሚሄድ ፓርቲዎቹ ይወስናሉ" ብለዋል።