በተሳታፊዎች ብዛት ክብረወሰን የሰበረው ኮፕ28
በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በአካልና በበይነ መረብ በመሳተፍ ላይ ናቸው
የኮፕ28 ተሳታፊዎች በግብጽ ሻርም አልሼክ ከተመዘገበው በእጥፍ ይበልጣሉ
በአረብ ኤምሬትስ ዱባይ እየተካሄደ የሚገኘው 28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በተሳታፊዎች ብዛት ክብረወሰን ይዟል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በኮፕ28 ጉባኤ በአካል ለመሳተፍ 97 ሺህ 372 ሰዎች ተመዝግበዋል፤ 3 ሺህ 74 ሰዎችም ጉባኤው ላይ በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።
ይህም የጉባኤውን ተሳታፊዎች ቁጥር 100 ሺህ 446 በማድረስ በመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪክ ቀዳሚው ሆኖ ተመዝግቧል።
በግብጽ ሻርም አልሼክ በተካሄደው ጉባኤ 50 ሺህ፤ በ2021 በስኮትላንድ ግላስጎ በተካሄደው ኮፕ26 ደግሞ 38 ሺህ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያወሳል።
በዱባዩ የኮፕ28 ጉባኤ ከ195 ሀገራት የተወከሉ 51 ሺህ 695 ሰዎች ተሳትፈዋል።
ከ2 ሺህ 350 ድርጅቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ተቆጣጣሪዎች 25 ሺህ 360 ተወካዮች በጉባኤው ላይ መሳተፋቸውም ተገልጿል።
የጸጥታ ሰራተኞች፣ ጸሃፊዎች እና ቴክኒሻኖችን ጨምሮ 16 ሺህ 345 ሰዎች በጉባኤው ተሳትፎ በማድረግም አጠቃላይ የተሳታፊዎቹን ቁጥር 97 ሺህ 372 አድርሰውታል ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት።
ጉባኤው ገና ያልተጠናቀቀ እንደመሆኑና በጉባኤው ለመሳተፍ የተመዘገቡትን መሰረት በማድረግ የወጣ በመሆኑ አሃዙ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል።
ከህዳር 25 2016 ጀምሮ በዱባይ ሲቲ ኤክስፖ እየተካሄደ የሚገኘው ኮፕ28 ጉባኤ ህዳር 2 ቀን 2016 ይጠናቀቃል።