በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ላይ “የአለም ንግድ ቀን” ሲካሄድ በዱባይ የመጀመሪያው ይሆናል
28ኛውን የአለም ንብረት ለውጥ ጉባኤ እያስተናገደች የምትገኘው ዱባይ “የአለም ንግድ ቀን”ን የጉባኤው አንዱ አካል አድርጋለች።
የመንግስታቱ ድርጅት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ምክክር ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው “የአለም ንግድ ቀን” ንግድን የአየር ንብረት ዋነኛው አጀንዳ አድርጓል።
አለማቀፉ የንግድ ሰንሰለት በአየር ንብረት ለውጥ ያለው ድርሻ የሚዳሰስበት የምክክር መድረክ ህዳር 24 2016 ይካሄዳል።
በንግድ ሰንሰለቱ ላይ ያሉ የአቅርቦት ክፍተቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚኖራቸው ጫና የሚመከርበት የአለም ንግድ ቀን በንግድ ስርአቱ ውስጥ የታዳሽ ሃይል ልማት ምን መምሰል እንዳለበትም ውይይት ይደረግበታል ነው የተባለው።
“የአለም ንግድ ቀን” በኤምሬትስ የንግድ ሚኒስትር ዶክተር ታኒ ቢን አህመድ አል ዜዩድ እና በአለም ንግድ ድርጅት ዋና ጸሃፊ የበላይ ሰብሳቢነት ይመራል።
የመንግስታቱ ድርጅት የንግድ እና ልማት ተቋም፣ አለማቀፉ የንግድ ዘርፍ ምክርቤቶ እንዲሁም የአለም የኢኮኖሚ ፎረምም በስብሰባው ላይ የተለያዩ ምክረሃሳቦችን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
የአለም የንግድ ድርጅት በየካቲት ወር 2024 በአቡ ዳቢ ለሚያደርገው የሚኒስትሮች ጉባኤ መነሻ የሚሆኑና የአለማቀፍ የንግድ ስርአቱን የሚያቀላጥፉ ስምምነቶች እንዲደረሱም የህዳር 24ቱ የዱባይ ምክክር ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
በ”አለም የንግድ ቀን” ምክክር “አለማቀፉ የንግድ ስርአት የአየር ንብረት መዛባትን በሚቀንስ መልኩ እንዴት ይቀየስ?” የሚል ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ይደረግበታል።
የታዳሽ ሃይል ልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በንግድ ስርአቱ ላይ የሚያመጣው አወንታዊ ሚና ላይ ምክክር ተደርጎም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ነው የተገለጸው።
መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከካርበን ብክለት የጸዳና ዘላቂ እድገትን የሚያስመዘግቡ እንዲሆኑ ስለሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍም ውይይት ይደረጋል ተብሏል።