የዱባዩ ኮፕ28 ጉባኤ አጀንዳዎች
የ2023 የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ነገ በዱባይ ይጀመራል
በጉባኤው ለአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ሀገራት ስለሚደረገው ድጋፍ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል
28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በነገው እለት በአረብ ኤምሬትሷ ዱባይ ይጀመራል።
አል ዐይን ኒውስ ለጉባኤው ተሳታፊዎች እና የሀገራት ተደራዳሪዎች የቀረበውን የውይይት ሰነድ ተመልክቷል።
የተራራዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክክር የሚደረግበት ኮፕ28 በተሳታፊዎችና ጎብኝዎች ብዛት እንዲሁም ያሳልፋቸዋል ተብሎ በሚጠበቀው ውሳኔ ታሪካዊ እንደሚሆን የኮፕ28 ፕሬዝዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር ተናግረዋል።
የጉባኤው መክፈቻ
የኮፕ28 ጉባኤ በነገው እለት በይፋ ሲከፈት የኮፕ27 ፕሬዝዳንት የነበሩትና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ። ሚኒስትሩ ዶክተር ሱልጣን አል ጀበር የ28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት የአየርንብረት ለውጥ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን የጉባኤው ተሳታፊዎች በጭብጨባ እንዲገልጹም ያደርጋሉ።
በመቀጠልም የኮፕ28 ፕሬዝዳንት የጉባኤው አጀንዳዎች የሚያጸድቁ ሲሆን በ2026 እና 2027 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎችን የሚያዘጋጁ ሀገራት ምርጫ ይካሄዳል።
በጉባኤው የ167 ሀገራት መሪዎች እንደሚታደሙና ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን የጉባኤው ዋና ዋና አጀንዳዎችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፦
1. የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትና ኪሳራ፦ በአየር ንብረት ለውጥ ታዳጊ እና ድሃ ሀገራት ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል። በድርቅ፣ በጎርፍ እና በመሰል አደጋዎች ሚሊየኖች ለረሃብ ቢጋለጡም ዋነኞቹ የአየር ንብረትን የሚበክሉ ሀገራት ለተጎጂዎቹ እናደርገዋለን ያሉትን የ100 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በሚገባ አላቀረቡም። በዱባዩ ጉባኤም ይሄው ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጥብቅ ውሳኔዎች እንደሚደረስበት ይጠበቃል።
2. የፋይናንስ ጉዳይ፦ ለታዳሽ ሃይል ልማት እና ለሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ስራዎች ከበለጸጉት ሀገራት እና ከአለማቀፍ ተቋማት ሊቀርብ ስለሚገባው የፋይናንስ አቅርቦት የኮፕ28 ጉባኤ በስፋት ይመክራል። በግብጽ ሻርምአልሼክ የተደረሰው ስምምነት አፈጻጸም ተገግሞም የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ነው የሚጠበቀው።
3. የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ፦ በኮፕ27 ጉባኤ (ሻርም አልሼክ) የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትና ኪሳራን ለማካካስ ስለሚደረግ ድጋፍና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲደራደር የተሰየመው 29 አባላት ያሉት ኮሚቴ ለአምስት ዙር በአቡዳቢ ተገናኝቶ ጊዜያዊ ስምምነት ላይ ደርሷል። የአለም ባንክ በጊዜያዊነት ያስተባብረዋል የተባለው ፈንድ ጉዳይ በኮፕ28 ለሀገራት መሪዎች ቀርቦ ይመከርበታል ተብሏል።
4. የተራራዎች ብዝሃ ህይወት ጥበቃ፦ የኮፕ28 ጉባኤ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የተራራዎች ብዝሃ ህይወት ጥበቃ አጀንዳ አድርጎ በመምከር የመጀመሪያውን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በኮፕ28 ጉባኤ ከአለም ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች እንዲሁም ወጣቶች ጋር የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰው ስለሚገኘው ጉዳት በዝርዝር ይመከራል።
የሀይማኖት መሪዎች የሚሳተፉበት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ሀላፊነት በሚወሰድበት ሁኔታ የሚደረገው ውይይትም የኮፕ28 አካል ነው።
በዓለም የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ህዝቦች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ለመምከር የሚገኙባት ዱባይ፥ በተመድ የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታሪካዊ ሁነትን ታስተናግዳለች።
ከ97 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እና ከ400 ሺህ በላይ ጎብኝዎች የሚታደሙበት 28ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጉባኤ ከነገ ጀምሮ ለ12 ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል።