አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን እንድትቋቋም መሰረተ ልማቶች ሊገነቡ ይገባል ተባለ
መሰረተ ልማቶቹ አፍሪካዊያን ከአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እንዲያገግሙ ያግዛሉም ተብሏል
በዱባይ እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 ጉባኤ የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን እንድትቋቋም መሰረተ ልማቶች ሊገነቡ ይገባል ተባለ፡፡
በአረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የኮፕ28 አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የመጨረሻ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር በመምከር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ምድራችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስ ጉዳትን መቀነስ የሚያስችሉ ምክክሮች እና ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡
መጠቃለያ ቀን በወጣው አዲስ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን እንድትቋቋም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚያስፈልጋት ተገልጿል፡፡
አፍሪካዊያን ከሚደርስባቸው የአየር ንብረት ለውጥ በቶሎ እንዲያገግሙ እና እንዲቋቋሙ የመሰረተ ልማት ግንባታ አስፈላጊ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
አፍሪካ እንደ ሙቀት እና ከባድ አውሎንፋሶችን መከላከል እንድትችል የዓለማችን የገንዘብ ተቋማት የትራንስፖርት፣ የውሃ እና የሀይል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑ አፍሪካዊያን ማህበረሰቦች የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባልም ተብሏል፡፡