የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ማካካሻ ፈንድ መቋቋሙ ታሪካዊ ውሳኔ እንደሆነ ተገለጸ
የበለጸጉ ሀገራት በሚለቁት በካይ ጋዝ ያላደጉ ሀገራት ካሳ እንዲከፍሉ የሚጠይቀው ሀሳብ ከ20 ዓመት በፊት የተነሳ ነበር
ፈንዱ ከ2024 ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተገልጿል
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ማካካሻ ፈንድ መቋቋሙ ታሪካዊ ውሳኔ እንደሆነ ተገለጸ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የዓለም ሀገራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ጋር ይመክራል፡፡
ይህ ጉባኤ በተመድ አባል ሀገራት እየተዟዟረ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስተናጋጅነት በዱባይ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በፈረንጆቹ 1991 ላይ የመጀመሪያው የተመድ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሲካሄድ ቫኑዋቱ የተሰኘችው ደሴት ፕሬዝዳንት ሮበርት ቫን ሌሮፕ የበለጸጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች በሚለቁት ካርበን ጋዝ ምክንያት ያላደጉ ሀገራት መጎዳት የለባቸውም፣ እነዚህ ሀገራትም ላደረሱት ጉዳት ካሳ ሊከፍሉ ይገባል የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ነበር።
ለበርካታ ዓመታት ሲያጨቃጭቅ እና ወደ ስምምነት መምጣት ያልተቻለ ሲሆን ይህ ሀሳብ ከ31 ዓመት በኋላ ፍሬ ማፍራቱ ተገልጿል።
በዱባይ እየተካሄደ ባለው የኮፕ28 ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ማካካሻ ፈንድ እንዲቋቋም ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
የበለጸጉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለደረሰባቸው ጉዳት እውቅና እና ካሳ ለመስጠት የተቋቋመው ይህ ፈንድ ከ2024 ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚቀየር ተገልጿል።
የሀሳቡ አመንጪ እና የዓለም አነስተኛ ደሴቶች ህብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት አሜሪካዊው ሮበርት ቫን ሌሮፕ እንዳሉት ውሳኔው ታሪካው ነው ብለዋል።
የፈንዱ መቋቋም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተጎዱ ላሉ ታዳጊ የዓለም ሀገራት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛልም ተብሏል።
ከ31 ዓመት በፊት የበለጸጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች ላደረሱት ጉዳት ካሳ መክፈል አለባቸው ሲባል በርካታ ባለሙያዎች ትችቶችን እና ወቀሳዎችን ሲያቀርቡ እንደነበርም ተገልጿል።
ፈንዱ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የማሰባሰብ እቅድ ያስቀመጠ ሲሆን ከዚያም በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ሀገራት የጉዳት ካሳ እንደሚከፍል ይጠበቃል።