አረብ ኢሚሬትስ በ2023 የምታዘጋጀውን ኮፕ-28 አርማ ይፋ አደረገች
በአኒሜሽንና በምስል ያታገዘው አዲሱ አርማ በሁሉም ከኮፕ-28 ጋር በተያያዙ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል
ኮፕ-28 በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በዱባይ ኤክስፖ ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2023 የሚካሄድ ይሆናል
የአረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን በታህሳስ 2023 የሚዘጋጀውን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-28) አርማ ይፋ አድርገዋል።
በዓለም ቅርጽ የተሰራው የጉባኤው አርማ ሁላችንም "የአንድ ዓለም" ነዋሪዎች ነን በሚለው ጽንሰ-ኃሳብ ላይ በመመስረት ዲዛይን የተደረገ ነው።
በብርሃን እና ጥቁር አረንጓዴ ቀለሞች ያሸበረቀ እንዲሁም ከአየር ንብረት ድርጊት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ምልክቶችን ማለትም ሰዎች፣ ታዳሽ የኃይል ቴክኖሎጂ፣ የዱር አራዊት እና የተፈጥሮ አካላት ያካተተ ነው ተብሏል።
ዲዛይኑ አፋጣኝ የአየር ንብረት ርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረቶችን በአንድነት እና በማጣመር ሁሉም ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ግዴታዎችን በትብብር ለማሟላት በሚያስችል መንገድ ላይ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳያ በሚሆን መልኩ የተሰራም ነው።
በአኒሜሽንና በምስል ያታገዘው አዲሱ አርማ አዲስ በተጀመረውን የጉባኤው ድረ-ገጽን ጨምሮ በተባበሩት አረብ አሚሬትስ አስተናጋጅነት ከሚካሄደው ኮፕ-28 ጋር በተያያዙ ሁሉም ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ እንደሚውልም ተገልጿል።
በተያያዘ "አንድ ዘላቂ ዓለም" ወይም በእንግሊዝኛው “One Sustainable World” የሚለው የጉባኤው መሪ ቃል የመንግስት እና የግሉ ሴክተሮች ፣ የሳይንስ ማህበረሰብ ፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ ሴቶች እና ወጣቶች የሚወክሉ ምልክቶች የያዘ ነው ተብሏል።
የ ኮፕ-28 ጉባኤን መሰረታዊ መልእክቶችን የሚያረጋግጥ የትብብር ኮንፈረንስ ፣የተቀናጀ ጥረት እና በሰሜንና በደቡብ ሀገራት መካከል የውይይት ድልድይ መገንባት አስፈላጊነት ላይ እንዲሰራ የሚያነሳሳ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም መሪ ቃሉ የኮፒ-28 ጉባኤው ሁሉንም ባካተተ መልኩ ዓለም ልቀትን በመቀነስ ረገድ (ሚቲጌሽን)፣ “ማላመድ (አዳፕቴሽን)”፣ “ፋይናንሲንግ” እና “ኪሳራዎች እና ጉዳቶች” በሚሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ለማሳካት ያሰበውን እቅድ ወደ ተግባር እንዲለውጥና የሚሰጠውን ትኩረት እንዲያጎለብት የሚያግዝ ነው።
ኮፕ-28 በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በዱባይ ኤክስፖ ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2023 የሚካሄድ ይሆናል።