የድንጋይ ከሰል በታዳሽ ሃይል ካልተተካ የምድራችን ፈተና ይቀጥላል - ጉቴሬዝ
የተመድ ዋና ጸሃፊ በኮፕ28 ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የአለም መሪዎች ቁርጠኝነት እና ትብብር ሊያድግ ይገባል ብለዋል
የበለጸጉት ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ለሚጎዱ ሀገራት ለመለገስ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙም አሳስበዋል
የድንጋይ ከሰል ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ካልተደረገ የአለም ሙቀት መጨመሩን ይቀጥላል አሉ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።
የተመድ ዋና ጸሃፊው በኮፕ28 ጉባኤ ባደረጉት ንግግር፥ የአየር ንብረት ለውጥ ከአንታርቲካ እስከ ኔፓል ጉልህ ተጽዕኖውን እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“ከፍተኛው የአለም የሙቀት መጠን በዚህ አመት ተመዝግቧል፤ ወደ ከባቢ አየር የተለቀቀው ካርበንም ከፍተኛው ነው፤ ድርቅና ጎርፉም እየተባባሰ ሄዷል” ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፥ በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት መፈጸም አለመቻሉ ፈተናውን እያከበደው መሄዱን አብራርተዋል።
የአለም የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳይበልጥ የተደረሰው ስምምነት እንዲፈጸም የአለም መሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ትብብር ወሳኝ መሆኑንም በማንሳት።
በተግባር እየታየ ያለው ነገር ግን ከዚህ በተቃርኖ መቆሙን የገለጹት የተመድ ዋና ጸሃፊ፥ የአለም የሙቀት መጠን በ3 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዲጨምር የሚያደርጉ ተግባራት እየታዩ መሆኑንም አንስተዋል።
የአለማችን የከባቢ አየር ብክለት 80 በመቶውን የሚይዙት የቡድን 20 አባል ሀገራት ቀዳሚውን ድርሻ ወስደው እንዲሰሩም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
“የድንጋይ ከሰል መጠቀማችን ከቀጠልን እየነደደች ያለችውን ምድራችን ማዳን አንችልም” ያሉት ጉቴሬዝ፥ ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት የታዳሽ ሃይል ሽግግር መቀየስ እንዳለበት አብራርተዋል።
ከነዳጅና ጋዝ ኢንዱስትሪዎች በንጹህ ሃይል ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ከ1 በመቶ አለመብለጣቸውን በመጥቀስም ኩባንያዎቹ “ካረጀው አካሄድ ወጥተው” ዘላዊና ከብክለት የጸዳ መንገድን እንዲከተሉ አሳስበዋል።
ታዳጊ ሀገራት እነርሱ ባለፈጠሩት ችግር ገፈት መቅመሳቸውን ቀጥለዋል፤ ይሁን እንጂ ዋነኞቹ የችግሩ ፈጣሪዎች የድጋፍ እጃቸውን ለመዘርጋት ከብዷቸዋልም ነው ዋና ጸሃፊው።
ሀገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተፈተኑ ለሚገኙ ሀገራት ለመለገስ ቃል የገቡትን 100 ቢሊየን ዶላር የሚያቀርቡበትን መንገድ ግልጽ እንዲያደርጉም በመጠየቅ።
ሰሜንና ደቡብ ዋልታን “በቀውስ ያመሳሰላቸው” የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በስፋት ያነሱት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ለሀገራት መሪዎች (በተለይ ለበለጸጉት) ጠንከር ያለ የማሳሰቢያ መልዕክት አስተላልፈዋል።