እንግሊዝ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ደረሰች
ከሶስት አመት በፊት በጣሊያን ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን ኔዘርላንድስን 2 ለ 1 አሸንፏል
የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ እሁድ በበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ይደረጋል
እንግሊዝ ኔዘርላንድስን በማሸነፍ ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ደረሰች።
በዶርትሙንስ ሲግናል ኢዱና ፕርክ ምሽት 4 ስአት ላይ በጀመረው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ኔዘርላንድስ ዣቪ ሳይመንስ በ7ኛ ደቂቃ መሪ መሆን ችላ ነበር።
በጀርመን ካሳያቸው የጨዋታ እንቅስቃሴዎች በተሻለ የመጣው የጋሬዝ ሳውዝጌት ቡድን በ18ኛው ደቂቃ ያገኘውን አወዛጋቢ የፍጹም ቅጣት ምት ሃሪ ኬን ወደ ግብ ቀይሮት የመጀመሪያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ በተጠናቀቀበት (90ኛው ደቂቃ) ሃሪ ኬንን ተክቶ የገባው ኦሌ ዋትኪንስ ግብ አስቆጥሮ እንግሊዝ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችላለች።
እንግሊዝ የፊታችን እሁድ በበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም የሶስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኗን ስፔን ትገጥማለች።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ አመት ተራዝሞ በ2021 በተደረገው 16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ደርሳ የነበረችው እንግሊዝ በጣሊያን በመለያ ምት መሸነፏ ይታወሳል።
ሶስቱ አናብስት ትናንት ምሽት ያሳዩት ብቃት በበርሊኑ የፍጻሜ ጨዋታ ለስፔን እጅ ላይሰጡ እንደሚችሉ ያመላከተ ነው ተብሏል።
ስፔን እና እንግሊዝ እሁድ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ በአውሮፓ ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ የሚገናኙበት ነው።
እንግሊዝ በሁለቱ አሸንፋለች (በ1980 እና 1996)። ሁለቱ ሀገራት በ1950 የአለም ዋንጫ ተገናኝተው ስፔን በሪዮ ዴጄኔሮ እንግሊዝን 1 ለ 0 ማሸነፏን መረጃዎች ያወሳሉ።
ከቅርብ ጊዜ ግንኙነታቸውም በ2018ቱ የኔሽንስ ሊግ እንግሊዝ በሲቪያ ስፔንን 3 ለ 2 ያሸነፈችበት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው።
በክለብ ደረጃ ግን ስፔን ከእንግሊዝ የተሻለ ስኬትን አስመዝግባለች።
የስፔን ክለቦች ለፍጻሜ የደረሱባቸው ያለፉት ዘጠኝ የሻምፒዮንስ ሊግ እና 10 ዩሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታዎች በላሊጋው ክለቦች አሸናፊነት ተጠናቀዋል።
የስፔን ብሄራዊ ቡድን በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ለፍጻሜ የደረሰበት መንገድ በጭማሪ ስአት እና በመለያ ምቶች ፍጻሜ ከገባችው እንግሊዝ ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም።
በምድቧ የ2021 ሻምፒዮኗን ጣሊያን እና የ2018 የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዋን ክሮሽያ የረታው የልዊስ ዴላ ፎንቴ ቡድን፥ በሩብ ፍጻሜው አዘጋጇን ጀርመን፤ በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ የ2018 ሻምፒዮኗን ፈረንሳይ አሸንፎ ለፍጻሜ ደርሷል።
ስድስት ጨዋታዎችን መለያ ምት ሳይጠብቁ በማሸነፍ አዲስ ታሪክ ያጻፉት የስፔን ከዋክብት፥ 13 ጎሎችን በማስቆጠርም የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አግቢ ናቸው።
በ1964 ፣ 2008 እና 2012 የአውሮፓ ዋንጫን ወደ ማድሪድ የወሰደው የስፔን ብሄራዊ ቡድን አራተኛውን ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያው ለመሆን እሁድ እንግሊዝን ይገጥማል።
ኔዘርላንድስ እና ፈረንሳይ ደግሞ ቅዳሜ የደረጃ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።