በጽኑ ያልታመሙት በፍቃዳቸው በቤታቸው ተለይተው እንዲታከሙ ሊደረግ ነው
ማሻሻያው የጤና ስርዓቱን መሸከም ከማይችለው ጫና ለመጠበቅና በትክክል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለመስጠት ነው
ይህ ግን ታማሚዎቹ የሚችሉና የቤታቸው ሁኔታ የሚፈቅድ ከሆነ ብቻ ሊሆን የሚችል ነው
በጽኑ ያልታመሙት በፍቃዳቸው በቤታቸው ተለይተው እንዲታከሙ ሊደረግ ነው
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል ከወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎች ማሻሻያ ጋር በተያያዘ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ላይ ጫና እየተፈጠረ እንደሆነ አስታውቀዋል።
“ህክምናው በሚሰጥባቸው ማዕከላት እምብዛም ምልክቶችን የሚያሳዩ እና የማያሳዩ ታማሚዎች አሉ” ያሉት ሚኒስትሯ ማዕከላቱ እየሞሉ እና የጽኑ ህሙማኑ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ በጽኑ ያልታመሙት በፍቃዳቸው በቤታቸው ተለይተው እንዲታከሙ ሊደረግ እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህ ግን ታማሚዎቹ የሚችሉና የቤታቸው ሁኔታ የሚፈቅድ ከሆነ ብቻ ሊሆን የሚችል ነው፡፡
አብረዋቸው ያሉ ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው ሌሎች ሰዎች አብረዋቸው ከሌሉም ነው የሚሆነው፡፡
ይህን ሲያሟሉ በቤት ውስጥ ተለይተው በስልክ እንዳስፈላጊነቱም በባለሙያ የአካል ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡
ይህ መሆን የማይችል ከሆነ ደግሞ ቀደም ሲል ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ በህክምና ተቋማት ሳይሆን በለይቶ ማቆያነት በተዘጋጁ ሌሎች በዩኒቨርስቲዎች እንደተዘጋጁት አይነት ማዕከላት ውስጥ እስኪያገግሙ ድረስ እንዲቆዩ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ዶ/ር ሊያ “ከዚህ በኋላ ይህን እንደምንሰራ ለማሳወቅ እወዳለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጤና ስርዓቱን መሸከም ከማይችለው ጫና ለመጠበቅና በትክክል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ መስጠት ከማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ላለመግባት ሲባል እንደህ ዓይነቶቹን ለውጦች ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ነው የተናገሩት፡፡
በሽታውን በመቆጣጠር ረገድ ማህበረሰቡ ይበልጥ ኃላፊነትና ባለቤትነትን መውሰድ የሚኖርበት ጊዜ አሁን መሆኑንም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡
የጋዜጣዊ መግለጫው ተሳታፊ የነበሩት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው የቫይረሱ ታማሚዎች በአዲስ አበባ እና በክልሎች በተዘጋጁ በድምሩ ከ7 ሺ በላይ የህክምና ማዕከላት ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት 3 እና 4 ሳምንታት በጣም ጨምሯል፡፡ በአጠቃላይ ከተያዙት ሰዎች ቁጥር ሁለት ሶስተኛ ያህሉ በነዚሁ ሳምንታት የተያዙ ናቸው፡፡
2 ሺ 900 የሚሆኑት አሁንም በጤና ተቋማት ውስጥ ሆነው ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
“ይህ ከፍተኛ ጫናን ይዞ መጥቷል” ያሉት ዶ/ር ኤባ “ዝግጁ ያደረግናቸው ጤና ተቋሞቻችን አሁን ከሞላ ጎደል እየሞሉ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በላይ ለመሄድ የሚያስችል አቅምም ሆነ ዝግጁነት ስለሌለ ይህን ለውጥ ለማድረግ ስለመቻሉም ገልጸዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ማንኛውም ጤነኛ የሆነና ቫይረሱ በሰውነቱ ያለ ግለሰብ በቤቱ ይህንን ክትትል ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡
በፈቃደኝነትም ላይ ይመሰረታል፡፡
ከቀብር ስነስርዓት፣ በለይቶ ማቆያዎች ከሚኖር ቆይታ እና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ጤና ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዛሬ የተያዙትን ጨምሮ 4070 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ይገኛሉ።