ድርጅቱ ዲግዛሚታሶን በጽኑ የኮሮና ታማሚዎች ላይ ያመጣውን የመጀመሪያ ሙከራ ውጤት ተቀበለ
ዲግዛሚታሶን ከፈረንጆቹ 1960 ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ መድሃኒት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል
የዓለም ጤና ድርጅት ዲግዛሚታሶን በመተንፈሻ መሳሪያ ላይ ያሉ የኮሮና ጽኑ ታማሚዎችን ሞት መጠን በ1/3 ይቀንሳል ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት ዲግዛሚታሶን በመተንፈሻ መሳሪያ ላይ ያሉ የኮሮና ጽኑ ታማሚዎችን ሞት መጠን በ1/3 ይቀንሳል ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት ዲግዛሚታሶን በጽኑ ህመም ላይ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ህይወት ሊያድን ይችላል በማለት በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የተካሄደውን የመጀመሪያ ክሊኒካል ሙከራ በበጎ ተቀብሎታል፡፡ በመተንፈሻ መሳሪያ ላይ ያሉ ታማሚዎችን ሞት መጠን በ1/3ና ሲቀንስ ኦክስጂን ብቻ የሚፈልጉ ታማሚዎችን ሞት መጠን ደግሞ በ1/5 እንደሚቀንስ ድርጅቱ ገልጿል፡፡
የዲግዛሚታሶን ጥቅም በጽኑ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎቸ ላይ ሲታይ በቀላል ህመም ላይ ባሉ ታማሚዎች ላይ ግን አልታየም፡፡
“ኦክስጂን ለሚፈልጉና በቬንትሌተር የሚተነፍሱ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ሞት ሊቀንስ የሚችል የመጀመሪያ ህክምና” መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ “ይህ ትልቅ ዜና ነው፤ ይህ እንዲሆን ላደረጉ የዩኬ መንግስትን፣ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን፣ ሆስፒታሎችንና ታማሚዎችን እንኳን ደስ አላችሁ”ብለዋል፡፡
ዲግዛሚታሶን ከፈረንጆቹ 1960 ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን እብጠት መቀነስን ጨምሮ የተወሰኑ የካንሰር አይነቶችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል አንደነበር ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ መድሃኒቱ በአነስተኛ ዋጋ ብዙ ሀገራት የሚገኝ ሲሆን በተለያየ ቀመር በድርጅቱ መድሃኒት ዝርዝር ውስጥ ከፈረንጆቹ 1977 ጀምሮ ተመዝግቧል፡፡
ተመራማሪዎች የመጀመሪያ ሙከራዎችን ለዓለም ጤና ድርጅት አንዳጋሩት የገለጸው ድርጅቱ ሙሉ የመረጃ ትንታኔ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ መረጃ ትንታኔው ላይ በመተባበር መድሃኒቱ ኮሮና ቫይረስን ለማከም መቼና አንዴት ጥቅም ላይ መዋል አንዳለበት አስተያየት እንደሚሰጥ ጠቁሟል፡፡
ድርጅቱ ዛሬ በጄኔቫ ባካሄደው ስብስባ የኮሮና ቫይረስ መድሃኒትን በማጥናት ላይ ትኩረት ስጥቶ ተወያይቷል፡፡ይህ ግኝት ብዙ ናሙናዎች የመውሰድን አስፈላጊነትን ያሳየ ሲሆን ድርጅቱ የህይወት አድን መድሃኒት ለማግኘት ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር እሰራለሁ ብሏል፡፡