ስለ ኮሮና ቫይረስ የመጀመሪያውን ማስጠንቀቂያ የሰጠው ዶክተር በቫይረሱ ሞተ፡፡
ስለ ገዳዩ ኮሮና ቫይረስ መረጃ በመስጠት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የመጀመሪያውን ማስጠንቀቂያ የሰጠው ቻይናዊ ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ በቫይረሱ መሞቱን የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ ምንም መረጃ ባልነበረበት ወቅት እንደ አውሮፓውያኑ ታህሳስ 30 አብረውት በዉሃን ሆስፒታል የሚሰሩ ባልደረቦቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በተለያየ አማራጭ ዶክተሩ መልእክት አስተላልፏል፡፡
ይሄን ተከትሎ የ34 ዓመቱ ዶክተር ሊ ከፖሊስ ማስፈራሪያ ደርሶት እንደነበረ እና ሊከሰስ እንደሚችልም ተዘግቦ ነበር፡፡ ዶክተር ሊ የውሸት ወሬ አሰራጭቷል በሚል ነበር በፖሊስ የተወነጀለው፡፡
መረጃው እየተሰራጨ መምጣቱን ተከትሎ ሌሎችም በርካታ ሀኪሞች ከዶክተር ሊ በኋላ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
ይሁንና በወቅቱ ዝም ተብሎ የነበረው ቫይረሱ አሁን ላይ ከ28,300 በላይ ሰዎች ተጠቅተውበት የቫይረሱን አብሳሪ ዶክተር ሊን ጨምሮ ከ560 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን ተነጥቀውበታል፡፡
ዶክተር ሊ ስለኮሮና ቫይረስ ካወራ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነበር በቫይረሱ ተይዞ እንደ አውሮውያኑ ከጥር 12 ጀምሮ ህክምና ሲከታተል የቆየው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ባለስልጣን በዶክተር ሊ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን