የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከቀናት በኋላ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከሰሀራ በታች አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደርጉት ጉብኝት ኢትዮጵያን፣ ሴኔጋልንና አንጎላን እንደሚጎበኙ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
የፖምፒዮ የአፍሪካ ጉብኝት የሚደረገው የቀድሞው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ኢትዮጵያን ጨምሮ በ5 የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት ባደረጉ ልክ በሁለተኛው ዓመት ነው፡፡
ፖምፒዮ በሶስቱ ሀገራት ከየካቲት 7-11 በሚያደርጉት ቆይታ ከመሪዎቻቸው ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን በዳካር የሚጀምሩ ሲሆን በቆይታቸውም ከሴኔጋል መሪዎች ጋር የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚና የደህንነት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ይመክራሉ፤ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሞርጋን ኦርታጉስ እንዳስታወቁት፡፡
የአንጎላ ትኩረታቸው ደግሞ ሀገሪቱ የጀመረችውን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና የጸረ-ሙስና ትግል፣ አሜሪካ መደገፍ በምትችልበት ጉዳይ ዙሪያ መወያየት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቆይታቸው በዋናነት በታሪካዊው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሚኖራቸው ውይይት ሪፎርሙን ለማስቀጠል በትብብር ስለመስራት ይነጋገራሉ ሞርጋን በመግለጫቸው እንዳሉት፡፡
በአፍሪካ ህብረትም ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሀገራቸው ጠንካራ ወዳጅ ወደሆነችው ሳዑዲ አረቢያ ያቀናሉ፡፡ ቀጥሎም ኦማን የጉብኝታቸው ማሳረጊያ ሀገር ትሆናለች ነው የተባለው፡፡