በአምበጣ ወረርሽኝ ሳቢያ ሶማሊያ የአስቸኳይ ጊዜ አወጀች፡፡
የአምበጣ ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ ሰብል እያወደመብኝ ነው ያለችው ሶማሊያ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች፡፡
የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ቀድሞውንም ፈተና ውስጥ ያለው የሀገሪቱ የምግብ ዋስትና አሁን ይበልጥ አደጋ ላይ ወድቋል ብሏል፡፡
በቀጣዩ ሚያዝያ ወር ሰብል ከመሰብሰቡ በፊት በሀገሪቱ የአምበጣ ወረርሽኙ ሊቆም እንደማይችል ተገምቷል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በዚህ ልክ የበረሀ አምበጣ ወረርሽኝ ሲያጋጥማቸው የአሁኑ ከ25 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያቸው ሲሆን ኬኒያ ደግሞ የዘንድሮውን ያክል ወረርሽኝ ባለፉት 70 ዓመታት ገጥሟት አያውቅም፡፡
በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ መንጋው የአንዳንድ አርሶ አደሮችን ማሳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አውድሟል፡፡ አጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የችግሩ ሰለባ እንደሚሆኑ የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡
ይሁንና ክፍለ አህጉሩ የአስቸኳይ ጊዜ ያወጀችው ሶማሊያ ብቻ ነች፡፡
በቀጣናው የበረሀ አምበጣ ወረርሽኝን ለመከላከል የተባበሩት መንግስታት የእርሻና ምግብ ድርጅት ፋኦ በቅርቡ ዓለማቀፍ ድጋፍ መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር በአምበጣ የተወረረ አንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከጂቡቲ ድሬ ዳዋ የሚያደርገውን የበረራ አቅጣጫ ቀይሮ ቦሌ አየር ማረፊያ ለማረፍ መገደዱ ይታወሳል፡፡
አምበጣዎቹ በወቅቱ የአውሮፕላኑን ኢንጅን፣ አፍንጫውንና ክንፎቹን ወርረው የነበረ ሲሆን አውሮፕላኑ ቦሌ አየር ማረፊያ በሰላም አርፏል፡፡
በቀን እስከ 150 ኪሎ ሜትር የሚጓዙት አምበጣዎች እያንዳንዳቸው በየእለቱ የክብደታቸውን ያክል ይመገባሉ፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ