”በእገታው ምክንያት የሞተ ሰው ለመኖሩ ማረጋገጫ የለንም“
”በእገታው ምክንያት የሞተ ሰው ለመኖሩ ማረጋገጫ የለንም” -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በእገታው ምክንያት የሞተ ሰው የለም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ፊት ተገኝተው በህዳር ወር መጨረሻ ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደቤታቸው ሲሄዱ የታገቱ ተማሪዎችን አስመልክቶ ለተነሳለቸው ጥያቄ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መካለከያ ባደረገው አሰሳ “እሳከሁን የተገደለ ሰው የለም፤ ተጎድቶ የተገኘ የለም፡፡ ችግር አልደረሰባቸውም እንዳንል ደግሞ ቤተሰብ ጋር አልደረሱም፡፡ ”
በአሰሳው መሰረት መንግስት የታገቱ የሉም ለማለት የሚያስችል መረጃ ነበር፣ ነገር ግን “አልታገቱም “ የሚል መልስ መስጠት አልቻልንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፡፡
ለእገታው ኃላፊነት የወሰደ አካል ባለመኖሩና አጋቹ ካለበት የማይሰማና የማይናገር በመሆኑ ታጋቾችን ለማግኘት የሚደረገውን አሰሳ ፈታኝ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የመረጃና የመከላከያ ተቋማት አስፈላጊውን ሰራ እየሰሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመንግስት የመረጃ አሰጣጥ ፍጥነት ላይ ለተነሳላቸው ቅሬታ “ በአንድ በኩል ትክክል ነው፣ በሌላ በኩል ግን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ ታጋቾችን አደጋ ውስጥ ሊከት ይችላል” በሚል ስጋት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ታጋቾችን ለማግኘት ጥረት የሚያደርግ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙንና እገታው ከማንነት ጋር እንደማይገናኝና ይገናኛል የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳይደለም ገልጸዋል፡፡