የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር 170 ደረሰ
በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በቻይና 7736 ሲደርስ ከቻይና ዉጭ 88 ሰዎች ሰለባ ሆነዋል፡፡
በቻይና 124 ሰዎች ከበሽታው አገግመው ከሆስፒታል እንደወጡም ተዘግቧል፡፡
ቫይረሱ በሁሉም የቻይና ግዛቶች የተዛመተ ሲሆን ከቻይና ውጭ ደግሞ 17 ሀገራት በቫይረሱ ተነካክተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በኮሮና ቫይረስ ዓለማቀፍ ስጋትነት ዙሪያ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በዚህም ቫይረሱ ዓለማቀፍ ስጋት መሆን አለመሆኑ ይወሰናል ነው የተባለው፡፡ቫይረሱ ከተዳረሰባቸው ሀገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምታከናውናቸውን ተግባራት ያደነቀው ደርጅቱ ሁሉም ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በተጠንቀቅ እንዲቆሙም አሳስቧል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም በአንዳንድ ሀገራት የቫይረሱ ስርጭት፣ በተለይም ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ፣ እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ትናንት ገልጸዋል፡፡
በቻይና ናንጂንግ እኤአ ከመጋቢት13-15 ቀን 2020 ይደረግ የነበረው የዘንድሮው የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናም እንራዘም ተወስኗል፡፡
ናንጂንግ የውድድሩ ስፍራ
የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን ባወጣው መግለጫ ቻይና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥረት እያደረገች ቢሆንም ቫይረሱ አሳሳቢነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ውድድሩ በዚህ ወቅት በናንጂንግ አይካሄድም ብሏል፡፡ ውድድሩ በመጪው ዓመት መጋቢት ወር 2021 ላይ እንዲካሄድ ከናንጂንግ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ብሏል ፌደሬሽኑ በመግለጫ፡፡
በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከቻይና ዉሀን ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተለያዩ የዓለማችን አየር መንገዶችም ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ አሁንም በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክኒያቱ አንድም ለጥንቃቄ ሲሆን ሌላም ከተለያዩ ሀገራት ወደ ቻይና የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር መቀነስ ነው፡፡
ባጠቃላይ ቫይረሱ በዓለም ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው የቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጉዳትም እየበረታ ነው፡፡
የቫይረሱ መነሻ የዉሀን ከተማ የዱር እና የባህር እንስሳት ገበያ ሲሆን ተመራማሪዎች ምንጩ የሌሊት ወፍ ሊሆን እንደሚችል እየጠቆሙ ነው፡፡
የሌሊት ወፎች የብዙ ቫይረሶች መገኛ እና ምንጭ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የተለያዩ ዓለማቀፍ የዜና አውታሮች የዘገባው ምንጭ ናቸው፡፡