ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ አለማቀፍ ስጋት ሲጨምር የቻይና ኢኮኖሚ እየተጎዳ ነው፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካሁን 132 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል፡፡ ሁሉም ሟቾች ቻይናውያን ናቸው፡፡
የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው ደግሞ ከትናንቱ በ1,500 ያክል ጨምረው በቻይና 5,997 ሲደርሱ ከነዚህም 1,239 የቫይረሱ ተጠቂዎች በጸና የታመሙ ናቸው፡፡ ከቻይና ውጭ ደግሞ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 65 ሆንዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቻይና 9,239 ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ተጠርጥረዋል፡፡
አሁን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እኤአ በ2002 እዚያው ቻይና ተከስቶ ወደተለያዩ ሀገራት ተሰራጭቶ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ከነበረው ሳርስ (SARS) የተባለ የወፍ ጉንፋን ቫይረስ ተጠቂዎች በልጧል፡፡ በ2003 የሳርስ ተጠቂዎች ቁጥር 5,327 ነበር፡፡ የሳርስ ሟቾች ቁጥር ግን 349 ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የኮሮና ቫይረስ ሟቾች እስካሁን 132 ቢሆንም በየእለቱ ቁጥሩ እየጨመረ መሆኑ ሲታይ ገዳይነቱ ከሳርስ ሊበልጥ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ‘ሰይጣን’ ያሉትን ቫይረስ ቻይና ግን ታሸንፈዋለች ብለዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ጋር ባደረጉት ውይይት ዓለማወፍ የጤና ኤክስፐርቶች ወደ ቻይና እንዲገቡ ተስማምተዋል፡፡
የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን አንድ ኤክስፐርት እንዳሉት የቫይረሱ ፈጣን ስርጭት ለቀጣዮቹ 10 ቀናት ሊቀጥል ይችላል፡፡
የመተንፈሻ አካላትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃው ኮሮና ቫይረስ እስካሁን ምንም አይነት መድሀኒትም ሆነ ክትባት አልተገኘለትም፡፡ የቻይናን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የህክምና ጠበብቶች ግን የመድሀኒት ፍለጋ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ጃፓን 206፣ አሜሪካ ደግሞ 240 ዜጎቻቸውን በመጀመሪያ ዙር በረራ ከቻይና ዉሀን ወደ ሀገራቸው መልሰዋል፡፡
ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የቻይና ኢኮኖሚ ጉዳት እያጋጠመው መሆኑም ተዘግቧል፡፡ እንደ ማካኦ ባሉ የራስ ገዝ አስተዳደር የቻይና ግዛቶች የቱሪዝም ፍሰት እስከ 73.6 በመቶ ቀንሷል፡፡
በቫይረሱ ስጋት የተነሳ ወደ ቻይና የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ አንዳንድ የአሜሪካና የእንግሊዝ አየር መንገዶችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ ሀገሪቱ የሚያደርጉትን በረራ ቀንሰዋል፡፡
የብሪታኒያ አየር መንገድ ይባስ ብሎ ጥንቃቄ ለማድረግ በሚል ወደ ቻይና ዋና ግዛት የሚደረግ በረራን ሙሉ በሙሉ አቁሟል፡፡
የቻይናን ዋና ግዛት ጨምሮ በሆንግ ኮንግ አንዳንድ አካባቢዎች የእለት ፍጆታ አቅርቦቶችም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ሱፐር ማርኬቶች በአብዛኛው ባዶ ሆነው ነው የሚውሉት፡፡
የቫይረሱን ስርጭት በፍጥነት መግታትና በሽታውን መቆጣጠር ካልተቻለ፣ በህዝብ ብዛት የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀገር ቻይና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቷ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የተለያዩ ዓለማቀፍ የዜና አውታሮችን ለዘገባው በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡