እስካሁን 213 ሰዎችን ገድሎ 10,000 ሰዎች የተያዙበት ኮሮና ቫይረስ ዓለማቀፍ ስጋት ተብሏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ኮሮና ቫይረስን አስቸኳይ ምላሽ የሚያስፈልገው ዓለማቀፍ የጤና ስጋት ብሎታል፡፡
ከቻይና ተነስቶ በመላው ዓለም በፍጥነት እየተዛመተ መምጣቱ ነው ቫይረሱን ዓለማቀፍ ስጋት ያስባለው፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም የቫይረሱን ዓለማቀፍ ስጋትነት በመጠቆም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ምክኒያት በዋናነት ቫይረሱ ደካማ የጤና ስርዓት ባለባቸው ሀገራት ከተዛመተ ጉዳቱ እጅግ ሊያይል እና ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ስለሚችል ነው ብለዋል፡፡
የዋና ዳይሬክተሩን መግለጫ ተከትሎ ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር ዓለማቀፍ ድጋፍ ጠይቃለች፡፡
በተባበሩት መንግስታት የቻይና ቋሚ ተወካይ ዣንግ ጁን የቫይረሱ ስርጭት ባለበት እንዲገታ ዓለማቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ቫይረሱ ዓለማቀፍ ስጋት መሆኑ ቢታወጅም፣ የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ኮሚቴ ወደ ቻይና የሚደረጉ ጉዞዎች እና ከሀገሪቱ ጋር የሚደረጉ ንግዶች ያለመስተጓጎል መቀጠል እንዳለባቸው ያምናል ሲሉም ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሀገሪቱን እንደማግለል የሚቆጠር ተግባር በዓለማቀፉ የጤና ደንብ አንቀጽ 3 ከተደነገገው ሀሳብ ጋር የሚጻረር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ቻይና ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት እጅግ የሚደነቅ እና መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ሀገሪቱ ቫይረሱን የመቆጣጠር አቅም አላት ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የተለያዩ ሀገራት አሁንም ዜጎቻቸው ወደ ቻይና እንዳይሄዱ እያስጠነቀቁ ነው፡፡ ከነዚህ ሀገራት አንዷ የሆነችው ዩኤስ አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ቻይና እግራቸውን እንዳያነሱ በጥብቅ አሳስባለች፡፡
በርካታ አየር መንገዶችም ወደ ሀገሪቱ የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸውን ቀጥለዋል፡፡ የበረራ እገዳውን ከአፍሪካ ግብጽና ኬኒያም ተቀላቅለዋል፡፡
ቫይረሱ ከተከሰተባት የሀገሪቱ ከተማ ዉሀን ዜጎቻቸውን የሚያስወጡ ሀገራትም ጨምረዋል፡፡ ከተማዋ በአሁኑ ወቅት እንቅስቃሴ የሚባል ነገር እንደሌለባትም ነው መገናኛ ብዙሀን በመዘገብ ላይ የሚገኙት፡፡
በዓለም የተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ቻይናውያንም መገለል እየደረሰባቸው ነው ተብሏል፡፡ በመንገድ ላይ፣ በህዝብ ትራንስፖርቶች እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቻይናውያንን መሸሽ እየተለመደ መሆኑን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
እስካሁን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 213 ሲደርስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ደግሞ በቻይና ወደ10 ሺ ከቻይና ውጭ ደግሞ ከ100 በላይ ሆነዋል፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት በአንድ ቀን ልዩነት 2,000 ያክል ጨምሯል፡፡
የተለያዩ ዓለማቀፍ የዜና አውታሮች የዘገባው ምንጭ ናቸው፡፡