በርካታ ሰዎች ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመጓዝ ትራንስፖርት ፍለጋ እየተንገላቱ ነው
በርካታ ሰዎች ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመጓዝ ትራንስፖርት ፍለጋ እየተንገላቱ ነው
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር በተያያዘ በክልሎች እና በፌደራል መንግስት የተለያዩ የመከላከያ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያውጁ፣ ሌሎች የተለያዩ ክልሎች ደግሞ በተለያየ መጠን የነዋሪዎቻቸውን እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ የትራንስፖርት እገዳ ጥለው ቆይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በትናንትናው እለት የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ጥለው በቆዩት እገዳ ላይ ማሻሻያዎችን አድርገዋል፡፡ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዳግም እንዲጀመር የወሰኑት ክልሎቹ የተሳፋሪዎች ቁጥር ግን ሀገር አቀፉ አዋጅ በሚደነግገው መሰረት እንዲሆን ወስነዋል፡፡
የእገዳዎችን መነሳት ወሬ የሰሙ በርካታ ዜጎችም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ትራንስፖርት ፍለጋ ሲንገላቱ ተመልክተናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ መናኸርያዎች አንዱ በሆነው የላም በረት መናኸርያም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመጓዝ የተነሱ በርካታ ዜጎች ጓዛቸውን እንደሸከፉ በመናኸርያው ዙሪያ አንዣበዋል፡፡ ማህበራዊ ጥግግት እንዲቀር ሌት ተቀን በሚነገርበት በዚህ አስከፊ ጊዜ በስፍራው ያየናቸው ትራንስፖርት ፈላጊዎች ስለቫይረሱም ይሁን ስለመከላከያ መንገዱ ግንዛቤው ያላቸው አሊያም ግድ የሚሰጣቸው አይመስሉም፡፡ ከፍተኛ ጥግግት፣ ከወትሮው ያልተለየ መስተጋብር በስፍራው ይስተዋላል፡፡
ከትራንስፖርት ፈላጊዎቹ ብዙዎቹ ስራ በመፍታት አሊያም በማጣት ምክንያት ወደየቀዬያቸው የሚመለሱ፣ የተቀሩት ለበዓል ቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ የሚሄዱ፣ አንዳንዱም ለተለያዩ ጉዳዮቻቸው ከአካባቢያቸው እንደወጡ ከትራንስፖርት መቋረጥ ጋር በተያያዘ ከርመው መመለስ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ከወቅታዊው ቀውስ ጋር ተዳምሮ ትራንስፖርት አግኝተው መጓዝ ብቻ የተሳፋሪዎቹ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ወደ ደሴ ለመሄድ ትራንስፖርት ፍለጋ መጥቶ በስፍራው ያገኘነው ወጣት ግርማዬ አስጨናቂ እንዳጫወተን ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር በተያያዘ የቀን ስራውን ካጣ ሁለተኛ ወሩን ይዟል፡፡ ወጣቱ የቤት ኪራይ የሚከፍልበት፣ ህይወቱን በአዲስ አበባ የሚመራበት ገንዘብ የለውም፡፡ በመሆኑም ቤተሰቦቹ ጋር በመሄድ ይሄን ጊዜ ከእነርሱ ጋር ለማሳለፍ ወስኖ ትራንስፖርት ዛሬ ሚያዝያ 07/2012 ዓ.ም ይጀመራል የሚል ጭምጭምታ በመስማት ማልዶ ነው ወደ መናኸርያው የመጣው፡፡ ወጣቱ “ከኮሮና ይልቅ የገንዘብ እጦቴ እና ድህነቴ ያሳስበኛል” ይላል፡፡ ትራንስፖርት አግኝቶ ቤተሰቦቹ ጋር መሄድ ለእርሱ ከምንም በላይ ነው፡፡
ወጣት ግርማዬ አስጨናቂ
ሌሎች ያነጋገርናቸው ተስፈኛ ተሳፋሪዎችም እንዲሁ ዛሬ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር ሰምተው ወደ መናኸርያው መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፡፡ ተሳፋሪዎች እንዳወጉን አልፎ አልፎ እስከ ሸኖ ድረስ ብቻ ትራንስፖርት ይገኛል፡፡ ከዛ ውጭ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡
በስፍራው ካናገርናቸው ትራንስፖርት ፈላጊዎች አንዷ (የቤት ሰራተኛ የነበረች እና ወደ ቤተሰቦቿ የምትመለስ)
ስማቸውን ያልነገሩን የላም በረት መናኸርያ አመራር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ይጀመራል ተብሎ እንደነበር ገልጸውልናል፡፡ ይሁን እንጂ ለምን እንዳልተጀመረ ብንጠይቃቸው ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው የትራንስፖርት ሚኒስቴር እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በጉዳዩ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ለማናገር ብንሞክርም ሊሳካልን አልቻለም፡፡
ምንም እንኳን የትራንስፖርት አገልግሎት ባይኖርም ትራንስፖርት ፈላጊዎች ግን የመናኸርያ ደጆችን በመጥናት ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ከሚደርስባቸው መጉላላት ባለፈ ምንም ዓይነት ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ደግሞ ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸውን የሚያሰፋ ነው፡፡
አንዳንድ ክልሎች ወደ ግዛታቸው የሚደረግ ጉዞን አሁንም ድረስ አያስተናግዱም፡፡ ቢያስተናግዱ እንኳን ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰዎች ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ያስገድዳሉ፡፡ በመሆኑም ከየክልሎቹ ጋር በመናበብ የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የማህበረሰቡን እንግልት ለመቅረፍ እና ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ያጋሩን ግለሰቦች ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ባልተረጋገጡ መረጃዎች ለእንግልት ከመዳረጉ በፊት ከመንግስት ትክክለኛ መረጃ ሊደርሰው እንደሚገባም እንዲሁ፡፡