በረዶው የተፈጠረው “ኮሙሎኒምበስ” በሚባል ደመና መፈጠር ምክንያት እንደሆነ ጫሊ ገልጸዋል
በረዶው የተፈጠረው “ኮሙሎኒምበስ” በሚባል ደመና መፈጠር ምክንያት እንደሆነ ጫሊ ገልጸዋል
በትናንትናው እለት በኦሮሚያ ክልል በምእራብ አርሲ ኮፈሌ ከባድ በረዶ ያስከተለ ዝናብ ዘንቦ ነበር፡፡ ዝናቡን ተከትሎ የተከመረው በረዶ በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው የተጋራ ሲሆን ብዙዎች በበልግ ወቅት ከዚህ በፊት ያልተለመደ እንግዳ ክስተት ነው ሲሉት ነበር፡፡
ነገርግን የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ መደበኛና የሚጠበቅ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የኤጀንሲው የአየር ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ ለአል-አይን አማርኛ እንደተናገሩት በረዶው የተፈጠረው “ኮሙሎኒምበስ” በሚባል ደመና መፍጠር አማካኝነት ነው፡፡
እንደ ጫሊ ገለጻ “ኮሙሎኒምበስ” ደመና ከስር ጥቁር የሆነ ሲሆን የሚፈጠረውም በፀኃይ ኃይል ታግዞ ነው ብለዋል፡፡
“ደመናው በታችኛው ክፍል ጥቁር የሆነ ክምር ደመና የሚያስከትለው ነው፤ ይህ ደመና ከሌላኛው ደመና ጋር በሚጋጭበት ጊዜ መብረቅና ዳመና የሚፈጥረበት ሁኔታ አለ፡፡ በረዶም ይከሰታል”
በረዶ ከዚህ በፊትም በዚህ ወቅት በተለያየ ቦታ ተከስቶ ያውቃል ብለዋል ጫሊ፡፡
ጫሊ ዘንድሮ “ከህንድ ውቅያኖስ ጥሩ እርጥበት መጥቷል፡ በዚህ ምክንያትም በደቡብ ኢትዮጵያ ዝናብ እየአነበ ይገኛል” ብለዋል፡፡
ዝናቡ ለ20 ደቂቃ ያህል መዝነቡን የተናገሩት ጫሊ ያስከተለው ጉዳት ስለመኖሩ ሪፖርት እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡
የሚትሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ለምእራብና ለደቡብ ኦሮሚያ ዋና የዝናብ ወቅታቸው ነው፤ “ሰለዚህ ዝናቡ ወቅቱን ያልጠበቀ ሳይሆን በበልግ ወቅት የተገኘ ከባድ ዝናብ ሊባል ይችላል” ብለዋል፡፡
በረዶም ቢሆን በበልግ ወቅት ሊከሰት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡