ከቻይና ውጭ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሀገራት ከቻይና በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ሪፖርት እያደረጉ ነው
ከቻይና ውጭ ያሉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ሀገራት ከቻይና በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ሪፖርት እያደረጉ ነው
በደቡብ ኮሪያ ከ1,260 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 12 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡ በጣሊያን ከ320 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ 11 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በኢራን ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታውን ጨምሮ 139 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ 19 ሞት ተመዝግቧል፡፡
ፈረንሳይ አንድ ዜጋዋ በቫይረሱ መያዙን ስታረጋግጥ፣ ግሪክ ደግሞ ቫይረሱ ደርሷታል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ደግሞ ቫይረሱ ከኢራን እየተሰራጨባቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከኢራን ሚጎራበቱት ድንበር የመዝጋት እና እነርሱን ጨምሮ ሌሎችም ዜጎቻቸው ወደ ኢራን እንዳይጓዙ በማገድ ላይ ናቸው፡፡
የባህሬን፣ የኩዌይት፣ የኢራቅ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ዜጎች በርካታ የሀገሩስጥና የውጭ ቱሪስቶች ለሀይማኖታዊ ጉብኝት ከሚመላለሱበት የኢራን ቆም የተሰኘ ግዛት ነው ቫይረሱን ይዘው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት፡፡
ቫይረሱ በኢራን መስፋፋቱን ተከትሎ ሀገራት የሚወስዷቸው እርምጃዎች ቀድሞውንም በብዙ ማእቀብ ዉስጥ የምትገኘውን ሀገር ክፉኛ እንዳይጎዳት ተሰግቷል፡፡ ይህ ያሳሰባቸው የኢራን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሀኒ “አሜሪካና ሌሎች ጠላቶቻችን የሀገራችንን ኢኮኖሚ ይበልጥ ለመጉዳት ቫይረሱን እንደመሳሪያ ሊጠቀሙ አይገባም፤ አሜሪካ በኛ ላይ ክፋት ከምታሴር የራሷን ታማሚዎች በአግባቡ ታስታምም” ሲሉ መናገራቸውን ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ባጠቃላይ ከቻይና ውጭ ከ2,800 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ የ45 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በቻይና ደግሞ እስካሁን 78,190 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 2,718 ሰዎች ሞተዋል፡፡
ከቻይና ውጭ ብዙ አዳዲስ ተጠቂዎች ሪፖርት እየደረሰው እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይና ውጭ ካሉ የቫይረሱ ተጠቂ ሀገራት ከቻይና በላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት መደረጉን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቴድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ ናቸው የተናገሩት፡፡
በቻይና ማክሰኞ ዕለት ሪፖርት የተደረጉት አዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር 411 ሲሆን በቀረው ዓለም ግን ቁጥሩ 427 ነበር ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ፡፡
በዓለም ዙሪያ አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር አሁን ላይ 80,980 ደርሷል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ በጣሊያን ፣ ኢራን እና ደቡብ ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ድንገተኛ መጨመር “እጅግ የሚያሳስብ” መሆኑን ገልጸው፣ ይሁንና ቫይረሱን አሁንም መቆጣጠር እንደሚቻልና ወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደማይደርስ ገልጸዋል፡፡
ለዘገባው የተለያዩ ምንጮችን ተጠቅመናል፡፡