ከቻይና ውጭ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን እና ኢራን በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
ከቻይና ውጭ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን እና ኢራን በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ
ከቻይና ውጭ ሳይታሰብ በድንገት ከፍተኛ ተጠቂዎች የተገኙባት ደቡብ ኮሪያ፣ በቫይረሱ የተያዙ ዜጎቿ ቁጥር 602 ሲደርስ ከነዚህም አምስቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ዛሬ እሁድ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንዳስታወቀው 46 ተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተለይተዋል፡፡
ከጠቅላላው የቫይረሱ ተጠቂዎች 309ኙ ወይም ወደ 55 ከመቶ የሚሆኑት በዴጉ ከተማ ከሚገኘው ሺንቾንጂ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል መሆናቸውን ባለስልጣናት ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ከ9,300 በላይ የቤተ እምነቱ ተከታዮች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እንዲደረግላቸው የሀገሪቱ መንግስት ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ባስተላለፉት መልእክት፣ ኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ በመሆኑ ሀገሪቱ ከፍተኛውን ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት በየቀኑ ከ 5,000 እስከ 6,000 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እየተደረገላቸው ነው፡፡
ጣሊያን
ሌላዋ ከቻይና ውጭ በቫይረሱ ምክኒያት ከፍተኛ ስጋት የገባት ሀገር ጣሊያን ነች፡፡ በሀገሪቱ እስከ ዛሬ132 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተለይተዋል፡፡ አብዛኛው ተጠቂዎች የሚገኙት ደግሞ በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ነው፡፡
ከቫይረሱ ስጋት ጋር በተያያዘ ሶስት የሴሪአ ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሀ ግብር መሰረት እንዳይከናወኑም ተሰርዘዋል፡፡
ጨዋታዎቹ ኢንተር ከ ሳምፕዶሪያ፣ አታላንታ ከ ሳሱሎ እና ሄላስ ቬሮና ከ ካግሊያሪ ያደርጉት የነበሩ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ይሄም በሀገሪቱ 132 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ተከትሎ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር መንግስት የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑን ሴሪአው በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡ ቫይረሱ በሰሜን ጣሊያን አሳሳቢነቱ በመጨመሩ ምክኒያት በቀጣናው የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው የተሰረዙት፡፡
የሀገሪቱ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጠንካራ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነኝ ብሏል፡፡
ከነገ (ሰኞ እለት) ጀምሮ በሎምባርዲ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አብዛኛው ህዝባዊ ኩነቶች እንዲቋረጡም ተወስኗል፡፡
ኢራን
የመካከለኛው ምስራቋ ሀገር ኢራን ደግሞ 43 የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተውባታል፡፡ 8 ዜጎቸዋ ደግሞ በቫይረሱ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኪያኑሽ ጃሃንፖርት እንዳሉት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 15 ተጠቂዎች ተለይተዋል፡፡ በኢራን ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በቅዱስ ከተማዋ ቆም ነው፡፡
ዋና ከተማዋን ቴህራንን ጨምሮ በ14 ግዛቶቿ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መንግስት ወስኗል፡፡ በሀገሪቱ የሚከናወኑ የእግር ኳስ ውድድሮች ደግሞ በዝግ ስታዲየም እንዲደረጉ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡
በቻይና እስካሁን የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር 2,445 ሲደርስ ከ77,000 በላይ ተጠቂዎች ይገኛሉ፡፡ 22,936 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸው ተዘግቧል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን