የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለርሀብ የሚጋለጠውን የዓለም ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ያሳድገዋል ተባለ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለርሀብ የሚጋለጠውን የዓለም ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ያሳድገዋል ተባለ
በአሁኑ ወቅት ዓለም አስከፊ የበሽታ ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ ቀውስም ጭምር ነው ያጋጠማት ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሌይ ገልጸዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት በማድረግ ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተደረገ ውይይት ወቅት ተናግረዋል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት 100 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ የህይወት አድን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በህይወት ለመቆየት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው የዓለም ህዝብ ቁጥር 135 ሚሊዮን እንደሚደርስ ዴቪድ ቤዝሌይ ይፋ አድርገዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ተጨማሪ 130 ሚሊዮን ሰዎችን ለከፋ ርሀብ እንደሚያጋልጥ አክለው ገልጸዋል፡፡
እናም ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለርሀብ ለተጋለጠው ህዝብ የህይወት አድን ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ፣ ለሶስት ወራት ያህል በየእለቱ 300,000 ህዝብ በርሀብ ምክንያት ለሞት ሊዳረግ ይችላል፡፡ ይህ ቁጥር በኮቪድ 19 ምክንያት የሚፈጠረውን ቀውስ እንደማያካትትም ነው የተናገሩት፡፡
ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 2019 ለከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የተዳረጉት ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 ሀገራት ናቸው፡፡ የመን፣ ዲ.አር ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬኔዙዌላ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ናይጄሪያና ሀይቲ በዓመቱ ዋነኛ የምግብ እጥረት ችግር የነበረባቸው ሀገራት ነበሩ፡፡ አሁንም ቀውሱ በነዚሁ ሀገራት ላይ ሊበረታ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የበረሀ አምበጣ ወረርሽኝ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ወቅታዊው ኮቪድ 19 የችግሩ መንስኤዎች እንደሆኑ በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ የዓለምን ህዝብ ከጥፋት ለመታደግ የመሪነቱን ሚና እንዲወጣ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው እና ቀዳሚው ተግባር ሰላምን ማስፈን እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የተመድ አባል ድርጅቶች ሰብዓዊ ቀውሱን ለመከላከል ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እንቅስቃሴ መጀመራቸውም ተመላክቷል፡፡
ምንጭ፡- ዩኤን ኒውስ