በደቡብ ኮሪያ ከቫይረሱ ያገገሙ 163 ሰዎች በድጋሚ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል
በደቡብ ኮሪያ ከቫይረሱ ያገገሙ 163 ሰዎች በድጋሚ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል
በደቡብ ኮሪያ ድጋሚ ምርመራ ከተደረገላቸው ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ ታማሚዎች መካከል 163 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ የሀገሪቱ የጤና ባለስልጣናት የዚህን ሚስጥር ለማወቅ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ብለዋል፡፡
በቻይናም ተመሳሳይ ክስተት ተመዝግቧል፤ ከቫይረሱ ያገገሙ አንዳንድ ግለሰቦች በዳግም ምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡
ይሄም ከቫይረሱ ያገገመ ሰው በድጋሚ ሊያዝ ይችላልን? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
በደቡብ ኮሪያ ካገገሙ በኋላ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ጥቂት ነው፡፡ ምንም እንኳን በሀገሪቱ ካገገሙት 7,829 ሰዎች መካከል ምን ያክሉ በድጋሚ እንደተመረመሩ ባይገለጽም፣ ምርመራ ከተደረገላቸው መካከል ግን 163 ሰዎች (2.1%) ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ዳግም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ጉዳይ ታዲያ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የተቃረበችውን ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ መላውን ዓለም እያስጨነቀ ነው፡፡
የደቡብ ኮሪያ የበሽታዎች መከላከል እና ቁጥጥር ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ክዎን ጁን ዉከ እንዳሉት በድጋሚ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 44 በመቶው ቀለል ያሉ ምልክቶች ቢታዩባቸውም ቫይረሱን ወደ ጤነኛ ሰዎች ስለማስተላለፋቸው ግን ምንም ማሳያ እስካሁን አልተገኘም፡፡ ስለቫይረሱ እስካሁን ሳይንቲስቶች የማያውቋቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ኮቪድ-19 ባለፉት አስርት ዓመታት ዓለም ከገጠሟት ፈተናዎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ም/ል ዳይሬክተሩ በሽታውን “በጣም ከባድና ፈታኝ” ብለውታል፡፡
ያገገሙ ሰዎች እንዴት በድጋሚ ቫይረሱ ሊገኝባቸው ቻለ ለሚለው ጥያቄ ዋነኛው ምክንያት ተብሎ የታመነው በዳግም ምርመራው ያልተወገዱ የቫይረሱ ቅሪቶች እየተገኙ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ቫይረሱ በድጋሚ የሚገኘው በምርመራ ስህተት ምክንያት ወይም ዳግም በማንሰራራት ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ያገገሙት እንዴት ዳግም ቫይረሱ ሊገኝባቸው ቻለ? ዳግም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሌሎችን ሊበክሉ ይችሉ ይሆን? ለሚሉትና መሰል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የደቡብ ኮሪያ ተመራማሪዎች ጥረት እያደረጉ ነው እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፡፡