የግብጽ የጦር አውሮፕላን የድጋፍ ቁሳቁሶችን ይዞ ወደ አሜሪካ አቅንቷል
የግብጽ የጦር አውሮፕላን የድጋፍ ቁሳቁሶችን ይዞ ወደ አሜሪካ አቅንቷል
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ ለአሜሪካ የህክምና ቁሳቁሶን እንዲላክ በወሰኑት ውሳኔ መሰረት ሀገሪቱ በጦር አውሮፕላን ቁሳቁሶችን መላኳ ተዘግቧል፡፡ ይህም አሜሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለማገዝና ወዳጅነትን ለማሳየት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ሲሲ፡፡
በከፍተኛ ደረጃ በኮሮና ወረርሽኝ እየተጠቃች ላለችው አሜሪካ ድጋፉ መላኩን ያስታወቁት የግብጽ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አምባሳደር ባሳም ራዲ ናቸው፡፡ ይህ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የዋሽንግተንና የካይሮን ግንኙነት እንደሚያጠናክረውም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ የግብጽ መንግስት በከሮና ቫይረስ የተጠቁ ወዳጅ ሃገራትን የመደገፍ ከፍተኛ ፍላጎት አለውም ነው ያሉት፡፡
ግብጽ ከሰሞኑ አራት ቶን የሀክምና ቁሳቁሶችን ከቻይና መቀበሏን የሃገሪቷ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በግብጽ የአሜሪካ አምባሳደር ጆናታን ኮሃን ለግብጽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ግብጽ ከዚህ በፊትም ለቻይና፣ጣሊያንና ሌሎች ሃገራት ድጋፍ መላኳን ይታወሳል፡፡
በአሜሪካ እስካሁን ከ 819 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን ከ 45 ሺ በላይ ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል ተብሏል፡፡ በግብጽ ደግሞ 3ሺ 490 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 264 ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡