ስፔንና ፈረንሳይ ጠንካራ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ
ስፔንና ፈረንሳይ ጠንካራ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ
ሁለቱ የአውሮፓ ሀገራት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የጣሊያንን ፈለግ በመከተል ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡
በቫይረሱ 191 ሰዎች በሞቱባት በስፔን ለአስፈላጊ የመድኃኒት እና መሰል ግብይት አሊያም ለስራ ካልሆነ በስተቀር ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ተከልክሏል፡፡
91 ሰዎችን በኮሮና ቫይረስ ባጣችው ፈረንሳይ ደግሞ ሲኒማዎችን፣ ካፌና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ አብዛኛው ንግድ ቤቶች እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡
ከ1,440 በላይ ሰዎችን በቫይረሱ ምክኒያት በማጣት፣ ከቻይና ቀጥሎ ከፍተኛውን ሞት ያስተናገደችው ጣሊያን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ እገዳ ማድረጓ ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ምንም አይነት ስብሰባ ማድረግም ተከልክሏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ስርጭቱ በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣበትን አውሮፓን የወረርሽኙ ዋና ማእከል ብሎ ፈርጇል፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡን በማነሳሳት እጅግ ጥብቅ እርምጃ ሊወሰዱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አውስትራሊያ እና ኒው ዝላንድ ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገራቸው የሚገባ ማንኛውም ሰው ለ 14 ቀናት ለይቶ ማቆያ እንዲገባ ወስነዋል፡፡
አሜሪካ በአውሮፓ ሀገራት ላይ በጣለችው የጉዞ እገዳ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአየርላንድ ሪፓብሊክም እንዲካተቱ ወስናለች፡፡
ቫይረሱ ቀድሞ በተከሰተባት ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ካለው ስርጭት ይልቅ ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መብለጥ ጀምሯል፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም ቫይረሱ በተሰራጨባቸው ከ 120 በላይ ሀገራት የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ 142,000 በላይ ሲደርስ የሟቾች ቁጥር ከ 5,400 በልጧል፡፡
በቻይና በቫይረሱ ከተጠቁ ከ 80,000 በላይ ሰዎች መካከል ከ 67,000 በላይ የሚሆኑት አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል፡፡
ቀሪዎቹ ከ 61,000 በላይ የሚሆኑ ተጠቂዎች ደግሞ ከቻይና ውጭ ቫይረሱ በተከሰተባቸው ሀገራት የሚገኙ ሲሆኑ በነዚህ ሀገራት ከ2,200 በላይ ሞት ተመዝግቧል፤ የተለያዩ ምንጮች እንደዘገቡት፡፡