በአፍሪካ ከ10 ሺ የሚልቁ የጤና ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተዋል
ከ14 የሰሃራ በታች ሃገራት ብቻ ሪፖርት ከተደረጉ የቫይረሱ ተጠቂዎች 5 በመቶ ያህሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው
በኢትዮጵያም ከአንድ መቶ ያላነሱ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው
በአፍሪካ ከ10 ሺ የሚልቁ የጤና ሰራተኞች በኮሮና ተይዘዋል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአፍሪካ በጤና ባለሙያዎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱንየዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡
ወረርሽኙ ባለሙያዎቹን ክፉኛ እየተፈተነ እንደሆነ ያስታወቀው ድርጅት በአህጉሪቱ 40 ሃገራት የሚገኙ ከ10 ሺ በላይ ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልጿል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የተጠናከሩ በቂ መረጃዎች ባይኖሩም ከ14 የሰሃራ በታች ሃገራት ብቻ ሪፖርት ከተደረጉ የቫይረሱ ተጠቂዎች 5 በመቶ ያህሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከ14ቱ ሃገራት በ4ቱ ደግሞ የ10 በመቶ የተጠቂነት ድርሻ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያም ጥቂት የማይባሉ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ለዚህ ባለሙያዎቹ ሚገለገሉባቸው ህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዲሁም የጥንቃቄ ጉድለቶች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በአህጉሪቱ ካሉ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አብዛኞቹ የጥራት ችግር እንዳለባቸውም ይነገራል፡፡
በአንዳንድ የአህጉሪቱ ሃገራት የቫይረሱ ስርጭት እና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሚያሳስብ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንም ገልጿል ድርጅቱ፡፡ ደቡብ አፍሪካ በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ ሃገራት ተርታ ትጠቀሳለች፡፡
በመላው ዓለም ደረጃም ቢሆን በቫይረሱ የሚጠቁ ባለሙያዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በቫይረሱ መያዛቸው በላቦራቶሪ ምርመራ ከተረጋገጠ 15 ነጥብ 5 ሚሊዬን ገደማ ሰዎች መካከል 10 በመቶ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ናቸው እንደ ድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ ገለጻ፡፡
ከ750 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙባት አፍሪካ የ115 ሺ ሰዎች ህይወት ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ አልፏል፡፡