በመላው ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ
በኮሮና ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ
በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 203 ሺ 308 መድረሱን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲና ወርልዶ ሜትርስ ቁጥራዊ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2 ሚሊዮን 923 ሺ 285 ደርሷል፡፡ በመረጃው መሰረት በዓለም ላይ በቫይረሱ ለህልፈት ከተዳረጉ 203 ሺ 308 ሰዎች መካከል 54 ሺ 265 ሰዎች የሞቱት በአሜሪካ ነው፡፡ አሜሪካን በመከተል የአውሮፓ ሃገራት ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይና ብሪታኒያ በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ሞት ያሰመዘገቡ ናቸው፡፡ 837 ሺ 531 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ማገገማቸውም ተሰምቷል፡፡
በአሜሪካ በ 24 ሰዓታት ውስጥ 48,529 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኙ
በትናንትናው እለት ብቻ በዩ.ኤስ. አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ 48,529 ሰዎች የተገኙ ሲሆን በዚሁ እለት 2,772 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡ እስከ ትናንት ምሽት በሀገሪቱ የኮሮና ታማሚዎች ቁጥር ባጠቃላይ 960,896 ደርሷል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዓለም በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ግማሽ የሚሆኑት አሜሪካውያን ናቸው ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ54,000 በላይ መድረሱን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩቨርሲቲ መረጃ ያሳያል፡፡
ቻይና በዉሀን የሚገኙ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ሁሉም ከሆስፒታል መውጣታቸውን ገለጸች
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ በሆነችው ዉሀን ከተማ፣ በሆስፒታሎች ውስጥ የነበሩ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች አገግመው ከሆስፒታሎች መውጣታቸውን የሀገሪቱ ጤና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
“በዉሀን እና በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የጋራ ጥረት ዛሬ ሚያዚያ 18/2012 ዓ.ም በዉሀን ሆስፒታሎች የነበሩ ሁሉም የኮቪድ-19 ታማሚዎች ተለቀዋል” ሲሉ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሚ ፌንግ ተናግረዋል፡፡
ቻይና ዉሀን
በቻይናዋ ዉሀን እስከ ትናንት ባጠቃላይ 46,452 የኮሮና ታማሚዎች ነበሩ፡፡ ዉሀን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የእንቅስቃሴ እገዳ ተጥሎባት የነበረች በዓለም የመጀመሪያዋ ከተማም ነበረች፡፡ ከ76 ቀናት እገዳ በኋላ አሁን ላይ በከተማዋ እንቅስቃሴዎች ወደ ቀድሞ ስፍራቸው ተመልሰዋል፡፡
ቻይና በትናንትናው እለት 11 የኮሮና ታማሚዎችን አገኘች
በኮሮና ቫይረስ መነሻዋ ሀገር ቻይና በትናንትናው እለት ከተደረጉ ምርመራዎች 11 ሰዎች ብቻ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የሀገሪቱ ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ዛሬ አስታውቋል፡፡ ከነዚህም አምስቱ ከውጭ የገቡ ሲሆኑ የተቀሩት በሀገር ውስጥ የተለዩ ናቸው፡፡ ትናንት ከተለዩት ታማሚዎች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሀገሪቱ ከሩሲያ ጋር ከምትዋሰንበት የሰሜን ምስራቅ ግዛቷ ሄይሎንግጂያንግ የተገኙ ናቸው፡፡ ይሄም ሀገሪቱ ካገገመች በኋላ ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ከሩሲያ እንዳይመጣባት ስጋትን አሳድሯል፡፡
ከ11ዱ ታማሚዎች በተጨማሪ ምልክት ያላሳዩ 30 የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡ ባጠቃላይ ምንም ምልክት ያላሳዩ 1,000 የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በህክምና ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
እንደ ጤና ኮሚሽኑ መረጃ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 82,827 ሲሆን 77,394 ሰዎች አገግመው ወጥተዋል፤ 4,632 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡
ህንድ በአንድ ቀን 1,990 የኮሮና ታማሚዎችን ማግኘቷን አስታወቀች
በህዝብ ቁጥር የዓለማችን ሁለተኛዋ ሀገር ህንድ በትናንትናው እለት 1,990 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ማግኘቷን የገለጸች ሲሆን ይሄም ከእስካሁኑ እለታዊ ሪፖርቷ ከፍተኛው ነው፡፡
የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው አስካሁን 625,309 የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 26,496 ደርሷል፡፡ ባጠቃላይ 824 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የህንድ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል እንደ አውሮፓውያኑ እስከ ግንቦት 3 የሀገሪቱ ህዝብ ከቤት እንዳይወጣ አግዶ፣ ዜጎች በቤታቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ህዝብ የሚገኝባት ኡታር ፕራዴሽ ግዛት ግን እገዳውን እስከ ሰኔ 30 (ለ2 ተጨማሪ ወራት ያክል) አራዝማለች፡፡
በጀርመን ለሶስተኛ ተከታታይ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀነሰ
ጀርመን ትናንትን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቅናሽ እያሳየ መምጣቱን ይፋ አድርጋለች፡፡ በትናንትናው እለት 1,737 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው አጠቃላይ የሀገሪቱ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 154,175 ደርሷል፡፡ ትናንት የሞቱትን 140 ሰዎች ጨምሮ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 5,640 ደርሷል፡፡
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን በማላላት ላይ ነች፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን