እስካሁን በመላው ዓለም ከ 600 ሺ በላይ ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ አገግመዋል
እስካሁን በመላው ዓለም ከ 600 ሺ በላይ ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ አገግመዋል
በዓለም በኮሮና ከተያዙ ሰዎች መካከል 600,296 ሰዎች ማገገማቸው ተሰማ፡፡ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,333,164 መድረሱም ታውቋል፡፡ በቫይረሱ የሞቱት ቁጥር 160,799 ደርሷል፡፡ በአሜሪካ ከ 39 ሺ በላይ፣ በጣሊያን ከ 23 ሺ በላይ፣ በስፔን ከ 20 ሺ በላይ፣በፈረንሳይ ከ 19 ሺ በላይ ሞት ተመዝግቧል፡፡
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ በአሜሪካ ከ33400 በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው ቅዳሜ እለት ብቻ በዩ.ኤስ አሜሪካ 38,903 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚሁ እለት ብቻ 1,849 ሰዎች መሞታቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡ በሀገሪቱ እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ 739 ሺ ያህል ሰዎች መካከል ከ39 ሺ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሲኤንኤን እና ዎርልዶ ሜትር ምንጮቻችን ናቸው፡፡
አሜሪካ የወታደሮቿን የእንቅስቃሴ እገዳ እኤአ እስከ ሰኔ 30 አራዘመች
ፔንታጎን እንዳስታወቀው የአሜሪካ መከላከያ ዲፓርትመንት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመስጋት እና የወታደሮችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሲባል የሀገሪቱ ወታደሮች እንቅስቃሴ ተገድቦ እንዲቆይ ወስኗል፡፡ ሀገሪቱ ባለፈው ወር ነበር ወታደሮቿ ለ60 ቀናት ከሀገር እንዳይወጡ ያገደችው፡፡
የመከላከያ ዲፓርትመንቱ መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን 3000 ያህል የሰራዊቱ አባላት በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡
“የዓለም ጤና ድርጅትን መደገፍ ዓለማቀፍ ትብብርንመጠበቅ ነው” የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ዓለም ኮቪድ 19ኝ በሚዋጋበት በዚህ ጊዜ የኣለም ጤና ድርጅትን እና የድርጅቱን ዳይሬክተር መደገፍ፣ የብዝሀነት እና የዓለም አቀፍ ትብብር ፍልስፍናን መደገፍ ማለት ነው ብለዋል፡፡ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት ከዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ጋር በስልክ ውይይት ባደረጉበት ወቅት መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የስልክ ውይይቱ የተደረገው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠውን ድጋፍ ማቋረጧን ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቻይና መንግስትና ህዝብ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ትራምፕ የአሜሪካ ድጋፍ እንዲቋረጥ ቢያደርጉም የሀገሪቱ ባለሀብቶች እና ለጋሽ ድርጅቶች ግን አሁንም ለድርጅቱ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ብሉምበርግ የተሰኘው የቀድሞው የኒው ዮርክ ከንቲባ ለጋሽ ድርጅት በዛሬው እለት ለድርጅቱ 8 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል፡፡