ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የበረሀ አምበጣ ወረራ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ምስራቅ አፍሪካን በመውረር ላይ የሚገኘውን የበረሀ አምበጣ ለመከላከል ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡
ፋኦ እንዳስታወቀው በትብብር መንጋውን ማስወገድ ካልተቻለ በቀጣናው ከፍተኛ የምግብ ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ሳይጠበቅ ድንገት በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ የተከሰተው የበረሀ አምበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡
በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ አንዳንድ አርሶ አደሮች ማሳቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመንጋው ወድሞባቸዋል፡፡
የአምበጣ መንጋው አሁን ደግሞ ወደ ዩጋንዳም እንደተዛመተ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ አጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የመንጋው ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገምቷል፡፡
በተለይ በቀጣዩ ሰኔ ወር ላይ የበረሀ አምበጣ መንጋው 500 እጥፍ ሊጨምር እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ምግብና እርሻ ድርጅት ስጋቱን ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ላለፉት 25 ዓመታት የአሁኑን ያክል በአምበጣ መንጋ ተወረው የማያውቁ ሲሆን ኬኒያ ደግሞ ከ70 ዓመታት በኋላ በዚህ ደረጃ ክስተቱ ሲያጋጥማት የመጀመሪያዋ ነው እንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡
የአምበጣ መንጋው ከየመን ተነስቶ በቀይ ባህር በኩል ነው በምስራቅ አፍሪካ የተሰራጨው፡፡ ህንድ፣ ፓኪስታንና ኢራንም የወረርሽኙ ተጋላጭ ናቸው እንደ ፋኦ መረጃ፡፡
የአምበጣ መንጋው በቀን እስከ 150 ኪ.ሜ የሚጓዝ ሲሆን እያንዳንዱ አምበጣ በየእለቱ የክብደቱን ያክል ይመገባል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ