የኮሮናን ፖለቲካዊ ማድረግ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳ ሩሲያ ገልጻለች
የሩሲያ ተመራማሪዎች እና የኮሮና ቫይረስ በተፈጥሮ የተከሰተ በሽታ እንጅ እንደሚናፈሰው ከቤተ ሙከራ ያመለጠ አለመሆኑን አስታወቁ።
የቫይረሱን መነሻ ለመፈለግ እና ለመከታተል የሚደረገው ጥረት ለፖለቲካ ጥቅም መዋል እንደሌለበትም ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ጉዳዩን ፖለቲካዊ ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚጎዳም የሞስኮ ፖለቲከኞች እና ባለሙያዎች መናገራቸውን የቻይና ማዕከላዊ ቴሌቪዥን (ሲጂቲኤን) ዘግቧል፡፡
የሩሲያ የጤና ኢኮኖሚክስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ላሪሳ ፖፖቪች ቫይረሱ በተፈጥሮ የመጣ መሆኑን ሁሉም ጥናቶች እንደሚያለክቱ ተናግረዋል።
ታዋቂ መሆናቸው የተገለጸው የሩሲያ የቫይረስ ተመራማሪዎች እና አጥኝዎች በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ በተፈጥሮ የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል። ተመራማሪዎቹ ይህንን ያሉት የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ቤተ ሙከራዎች አምልጦ የወጣ ነው በሚል የሚነገሩ ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት መሆኑም ተገልጿል።
በዓለም ጤና ድርጅት ተመራማሪ የሆኑት ሩሲያዊው ዲሚትሪ ላቭሮቭ “በማያጠራጥር ሁኔታ“ የኮሮና ቫይረስ በተፈጥሮ የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል። “ እኔ ሳይንቲስት ነኝ የማምነው የተነገረ ነገር ሳይሆን እውነትን ነው“ ሲሉ ተመራማሪው ተናግረዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድር ፑቲን ሃምሌ ወር ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኮሮና ክትባትነ ማፋጠን እና ኢኮኖሚን ማነቃቃት እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሞስኮ ኮሮናን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር አንሚያስፈልግ ገልጻ ይህንንም በፍጹም ለፖለቲካ ጥቅም እንደማታውለው አስታውቃለች፡፡
የሩሲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በነኩላቸው ምዕራባውያን የኮሮና ቫይረስን መነሻ ቦታ ማጣራትን ለፖለቲካ ጥቅም እያዋሉት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የቫይረሱን መነሻ ቦታ ማወቅ በሽታውን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ምንም ጥቅም እንደሌለውም ነው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ያስታወቁት፡፡
የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ያልተረጋገጡ ጉዳዮችን በማውራት ተቀባይነትን ለማግኘት እና ነጥብ ለማስቆጠር ማቀድ ትክክል እንዳልሆነም ሩሲያ በባለስልጣኖቿ እና በባለሙያዎቿ በኩል እየገለጸች ነው፡፡
ዓለም አሁን መተባበርና መነጋገር ያለበት ቫረሱን በጋራ መከላከል ላይ ሊሆን እንደሚገባም ነው ሞስኮ የገለጸችው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን መነሻ ምክንያት በቻይና ውስጥ ለማጥናት ያቀረበውን ጥያቄ ቤጅንግ ውድቅ ማድረጓን ከሰሞኑ ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ የኮሮና ቫይረስ መነሻ ምክንያትን ለመመርመር ለሁለተኛ ዙር ስራ ቻይናን ቢጠይቅም ሀገሪቱ ግን ፈቃደኛ አለመሆኗን የቻይና ምክትል የጤና ሚኒስትር መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ቤተ ሙከራዎች አምልጦ የወጣ ነው በሚል ቤጅንግን የሚወቅሱ እንዳሉ ሁሉ የሩሲያ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ቫይረሱ በተፈጥሮ የመጣ ነው እያሉ ናቸው፡፡