ኢትዮጵያ በ2022ቱ የሀገራት የሙስና ደረጃ ስንተኛ ላይ ተቀመጠች?
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባዳረገው ሪፖርት ኢትዮጵያ ከ100 ነጥብ 38 በማምጣት 98ኛ ደረጃን ይዛለች
አፍሪካዊቷ ሶማሊያ በ12 ነጥብ ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር በሚል ቀዳሚውን ደረጃ መያዟም ተገልጿል
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባደረገው ጥናት ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ 95 በመቶው የዓለም ሀገራት ሙስናን መዋጋት እንደተሳናቸው አመላክቷል።
ተቋሙ የ2022 የሀገራት የሙስና ተጋላጭነት ደረጃን ይፋ አድርጓል።
ሙስና እና አመጽ ያላቸውን ትስስር ያመላከተው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፥ "በሙስና የተደናቀፉ መንግስታት ህዝባቸውን የመጠበቅ አቅም የላቸውም፤ የህዝቡ ቅሬታም ወደ ብጥብጥ የመቀየር እድሉ ከፍተኛ ነው" ብሏል።
“ሙስና ዓለማችንን የበለጠ አደገኛ ቦታ አድርጎታል። መንግስታት በሙስና ዙሪያ በትብብር የሚያከናውኗቸው ስራዎች ውጤታማ አለመሆናቸው አሁን ያለውን አመጽና ግጭት ያባብሳል፤ እናም በሁሉም ቦታ ሰዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ” ሲሉ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሊቀመንበር ዴሊያ ፌሬራ ሩቢዮ ተናግረዋል።
አክለውም “ብቸኛው የመፍትሄ መንገድ በየደረጃው ያለውን ሙስናን ከስር መሰረቱ መንቀልና የመንግስት አገልግሎት ለሁሉም ሰዎች የሚደርስበትን አግባብ ማመቻቸት ነው” ብለዋል።
ሪፖርቱ ሀገራትን ከ"ከፍተኛ ሙስና" እስከ "በጣም ከሙስና የጸዱ" በሚል ከ100 ነጥብ ሰጥቶ በደረጃ አስቀምጧቸዋል።
ዴንማርክ በዚህ ዓመት 90 ነጥብ በማምጣት ዝቅተኛ ሙስና ያለባት ሀገር ተሰኝታለች።
ፊንላንድ እና ኒውዚላንድ ደግሞ 87 ነጥብ በማምጣት ይከተላሉ።
ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት እና የሰብዓዊ መብት መከበርም ሀገራቱ "ሰላማዊ" ከሚባሉት ዝርዝር ውስጥ እንዲሰለፉ ማድረጉን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ሪፖርቱ ምዕራብ አውሮፓ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ ቢሆንም አንዳንድ የአህጉሩ ሀገሮች ግን ከደረጃቸው የመውረድ አሳሳቢ ምልክቶች አሳይተዋል ነው ያለው።
እንግሊዝ አምስት ነጥቦችን በመውረድ ወደ 73ተኛ ዝቅ ብላለች፤ ይህም ለሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ ያነሰ ነጥቧ ነው መባሉን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ሪፖርቱ ህዝቡ በፖለቲካ ላይ ያለው እምነት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነውም ብሏል።
ለ180 ሀገሮች እና ግዛቶች ደረጃ የሰጠው የትራንስፓረንሲ ሪፖርት፤ ሶማሊያን በ12 ነጥብ ከፍተኛ ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር በሚል ቀዳሚውን ደረጃ ሰጥቷታል።
ደቡብ ሱዳንና ሶሪያ በ13 ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ሲይዙ፥ ቬንቩዌላ፣ የመን እና ሊቢያም ከባድ ሙስና ውስጥ በመዘፈቅ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ኢትዮጵያም 38 ነጥብ በማምጣት ከ180 ሀገራት 94ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አመላክቷል።
ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ሞሮኮ እና ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ እኩል 38 ነጥብ ተሰጥቷቸዋል።