2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የህዝብና የሀገር ሀብት በሙስና ባክኗል - የጸረ ሙስና ኮሚቴ
760 ጥቆማዎች ደርሰውኛል ያለው ኮሚቴው፥ በአዲስ አበባ ብቻ 26 ሺህ ካ.ሜ መሬት የሙስና ወንጀል ተፈጽሞበት መገኘቱን ገልጿል
መንግስት "አደገኛ ወረርሽኝ" ሆኗል ላለው ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ ባለፈው ህዳር አቋቁሟል
ሀገራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ እስካሁን ባከናወንኩት ተግባር በሙስና ምክንያት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት መባከኑን ደርሼበታለሁ አለ።
ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴው 759 የሙስና ወንጀሎች ከህብረተሰቡ በጥቆማ ቀርቦልኛል ያለ ሲሆን፤ ከጥቆማዎቹ መካከል 175 የሙስና ወንጀሎች በመለየት ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ነው ይፋ ያደረገው።
እስካሁን በ81 ወንጀሎች ላይ ክስ መመስረቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
640 የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ደግሞ ክስ በመመስረት ተጠያቂ እንደሆኑ ሰብሳቢው ገልጸዋል።
25 ሽህ 885 ካ.ሜ መሬት በአዲስ አበባ ከተማ የሙስና ወንጀል ተፈጽሞበት በምርመራ መገኘቱንም የጸረ ሙስና ኮሚቴው ሰብሳቢ መናገራቸውን የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።
ብሄራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴው ስራ እንደጀመረ በሰጠው መግለጫ፡ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ምዝበራው አሳሳቢ እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም።
175 ሺህ ካሬ መሬትና ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የመዘበሩ፣ በልማት ተነሺ ስም በሀሰተኛ ሰነድ መሬት የሰጡ እና የኮንዶሚኒየም ቤት የመዘበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩንም ገልጾ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም መሬት ነክ የሆኑ ጉዳዮችን አገልግሎት ለወራት አግዶ መክረሙ የሚታወስ ነው።
መንግስት "አደገኛ ወረርሽኝ" ሆኗል ላለው ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ስራ የጀመረው በህዳር ወር 2015 ነበር።
ኮሚቴው መንግስት በጥናት ለየኋቸው ያላቸውንና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችን እንዲመረምርና ለህግ እንዲያቀርብ ሃላፊነት ተሰጥቶታል።
ኮሚቴው ስራ እንደጀመረም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉ የሚታወስ ነው።