በ2024 የሀገራት የሙስና ደረጃ ኢትዮጵያ ስንተኛ ላይ ተቀምጣለች?
የ180 ሀገራትን የሙስና ተጋላጭነት በማጥናት ደረጃቸውን ይፋ የሚያደርገው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ2024 ሪፖርቱን አውጥቷል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/12/273-115516-funds-cash13_700x400.jpg)
ደቡብ ሱዳን በ2024 ቀዳሚዋ ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር መሆኗ ተጠቁሟል
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ሙስና በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
የ180 ሀገራትን የሙስና ተጋላጭነት በማጥናት ደረጃቸውን የሚያወጣው ተቋሙ የ2024 ሪፖርቱን ትናንት በጀርመን በርሊን ይፋ አድርጓል።
በዚህም ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት በደረጃው የተካተቱ ሀገራት ከ100 ነጥብ ከ50 በታች ማስመዝገባቸውን ነው የጠቀሰው።
አለማቀፍ አማካዩ 43 ነጥብ መሆኑም በዘርፉ ላይ አስቸኳይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጥ ግድ እንደሚል ማመላከቱን የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ዋና ስራ አስፈጻሚ ማይራ ማርቲኒ ተናግረዋል።
ዴንማርክ ከ100 ነጥብ 90 በማግኘት ለሰባተኛ ተከታታይ አመት ዝቅተኛ ወይንም ምንም ሙስና የማይታይባት ሀገር ሆናለች። ፊንላንድ እና ሲንጋፖር ደግሞ በ88 እና 84 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኒውዝላንድ፣ ሉግዘንበርግ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ እና ኦስትሪያ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የ2024 ሪፖርት ያመላክታል።
የባለፈውን አመት (37 ነጥብ) ያስጠበቀችው ኢትዮጵያ በአንድ ደረጃ ዝቅ ብላ 99ኛ ላይ ተቀምጣለች።
ደቡብ ሱዳን በ2024 ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር በመሆን በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ (180ኛ) ይዛለች።
ሶማሊያ፣ ቬንዙዌላ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያ እና ኤርትራ ከደቡብ ሱዳን በመከተል በደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
6 ነጥብ 8 ቢሊየን የአለማችን ህዝብ የሙስና ተጋላጭነት አመላካች ነጥባቸው ከ50 በታች በሆኑ ሀገራት ይኖራል። ይህም ከአለም ህዝብ 85 በመቶውን ይሸፍናል።
ባለፉት አምስት አመታት ሰባት ሀገራት ደረጃቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ችለዋል። እነዚህም ኮቲዲቯር፣ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ኮሶቮ፣ ኩዌት፣ ማልድቪስ፣ ሞልዶቫ እና ዛምቢያ ናቸው።
ሙስና እና የአየር ንብረት ለውጥ
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሀገራት የሙስና ተጋላጭነት አመላካች ጥናት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የሚመደብ በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ሀብት መዘረፉን አመላክቷል።
አብዛኞቹ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት በተቋሙ የሙስና ደረጃ ያስመዘገቡት ውጤት ከ50 በታች ነው። ደቡብ አፍሪካ፣ ቬትናም እና ኢንዶኔዥያ ለዚህ አበይት ማሳያ ሆነው ቀርበዋል።
በደቡብ አፍሪካ"ኢስኮም" ከተባለው የመንግስት የነዳጅ ድርጅት በየወሩ አንድ ቢሊየን ራንድ (56 ቢሊየን ዶላር) የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚመዘበር የተቋሙ የቀድሞው ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል ይላል ሪፖርቱ።
በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተጎዱ የሚገኙት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ቬንዙዌላ ያስመዘገቡት ነጥብ ከ8 እስከ 10 መሆኑም የሙስና እና የአየር ንብረት ለውጥ ትስስርን ያሳያል ተብሏል።