አስተናጋጇ ኮትዲቮር የውድድሩን የ2021 አሸናፊ የሆነችውን ሴኔጋልን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ተቀላቅላለች
ኮትዲቮር ሴኔጋልን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀለች።
ኮትዲቮር እና ኬፕ ቨርዴ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታ አልፈዋል።
የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ አስተናጋጇ ኮትዲቮር የውድድሩን የ2021 አሸናፊ የሆነችውን ሴኔጋልን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ተቀላቅላለች።
ትናንት ምሽት አምስት ሰአት በቻርስ ኮናን ባንይ ስቴዲየም በተካሄደው የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ጊዜ 1-1 አቻ ከጠናቀቁ በኋላ ወደ መለያ ምት አምርተዋል።
ሙሳ ናይ ካይቴ መለያ ምት በመሳቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሴኔጋል 5-4 በኮትዲቮር ተሸንፋለች።
ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ሳዲዮ ማኔ ከግራ በኩል ያሻገራትን ኳስ ሀቢብ ዲያሎ ወደ ግብ ቀይሮ ሴኔጋል መምራት ችላ ነበር።
ማኔ በዚህ ጨዋታ በሰራው ስህተት ቀይ ካርድ ከማየት ማምለጡ እድለኛ ቢያደርገውም፣
የ90 ደቂቃው ጨዋታ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ኮትዲቯር ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት በፍራንክ ከሲ አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር አቻ መሆኗ ሴኔጋልን ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል።
ኮትዲቮር በሩብ ፍጻሜ ውድድር ዛሬ ከሚካሄደው የማሊ እና ቡርኪናፋሶ ጨዋታ አሸናፊ ጋር በቀጣይ ቅዳሜ ትጋጠማለች።
ከቀናት በፊት ኮትዲቮሮች ከባድ ችግር ውስጥ ገብተው ነበር።
ኮትዲቮሮች በሜዳቸው ክብረወሰን በሆነ 4-0 በኢኳቶሪያል ጊኒ ተሸንፈው ለመሰናበት ጫፍ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት አሰልጣኝ ጅን ልዋስ ጋሴችን በረዳት አሰልጣኙ ኢመርሴ ፋኤ መቀየራቸው ይታወሳል።
ነገርግን እድለኞቹ ኮትዲቮሮች ወደ መጨረሻ 16 ቡድኖች ውስጥ እና ወደ ሩበ ፍጻሜ ማለፍ ችለዋል።
በተመሳሳይ ትናንት ምሽት ሁለት ሰአት በተካሄደ ጨዋታ ኬፕ ቨርዴም ማውርታኒያን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
የኬፕ ቨርዴው አምበል ርያን ሜንዴዝ የ90 ደቂቃው ጨዋታ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብ በመቀየሩ ኬፕ ቨርዴ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለች ትንሿ ሀገር ሆናለች።
በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋልን ጨምሮ ትላልቅ ስም ያላቸው ቡድኖች ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል አልቻሉም።