ግብጻዊው መሀመድ ሳላህ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አይሰለፍም ተባለ
እንደፌደሬሽኑ ከሆነ ሳላህ ግብጽ ከኬፕቨርዴ የምታደርገው እና ግብጽ ወደ 16ቱ የምታልፍ ከሆነ የሚኖራት ጨዋታ ያልፉታል
መሀመድ ሳላህ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ ምክንያት በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች እንደማይሰለፍ የግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል
ግብጻዊው መሀመድ ሳላህ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አይሰለፍም ተባለ።
መሀመድ ሳላህ ባለፈው ሀሙስ ግብጽ ከጋና ጋር 2-2 አቻ በተለያየችበት ጨዋታ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ ምክንያት በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች እንደማይሰለፍ የግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን(ኢኤፍኤ) አስታውቋል።
ፌደሬሽኑ ባወጣው መግለጫ "የኤክ ሬይ ምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየው ሳላህ የጡንቻ ጉዳት እንዳጋጠመው ስላረጋገጠ፣ በሚቀጥሉት ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አይሰለፍም" ብሏል።
እንደፌደሬሽኑ ከሆነ ሳላህ ግብጽ ከኬፕቨርዴ የምታደርገው እና ግብጽ ወደ 16ቱ ቡድን ውስጥ የምታልፍ ከሆነ የሚኖራት ጨዋታ ያልፉታል።
ባለፈው ሀሙስ እለት በቡድን "ቢ" ግብጽ ከጋና ጋር በአቢጃን ባደረገችው ጨዋታ፣ የጨዋታ ግማሽ ከመድረሱ በፊት ነበር የጡንቻ መሸማቀቅ ህመም ያጋጠመው።
በትናንትናው እለት ግብጻዊው ዶክተር መሀመድ አቡ ኢል ኢላ እንደገለጸው ሳላህ ህመሙ መጀመሪያ እንደተሰማው ጨዋታውን መቀጠል ፈልጎ የነበረ ቢሆንም ህመሙ ሲብስበት ከሜዳ ለመውጣት ጠይቋል።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ሳላህ ጉዳቱ ከበድ ያለ ሊሆን ይችላል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የ31 አመቱ ሳላህ በሊቨርፑል በቆየበት ከስድስት በላይ በሆነ የጨዋታ ዘመን ሳይጫወት የቀረባቸው 10 ሊግ ጨዋታዎች ናቸው።
ክሎፕ የሊቨርፑል የህክምና ቡድን የሳላህ ጉዳት ምንያህል እንደሆነ ለማወቅ ወደ ኮትዲቮር ስለመጓዙ እርግጠኛ አለመሆኑን ተናግሯል።
የሳላህን የምርመራ ውጤት አይተን እንወስናለን ብሏል ክሎፕ።
የሳላህ በጨዋታው አለመሰለፍ የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እና በዚህ ውድድር ደካማ የሆነ አጀማመር ላሳየችው ግብጽ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል ተብሏል።
ግብጹ ወደሚቀጥለው ዙር ለማለፍ በቀጣይ ሰኞ በምታደርገው ጨዋታ ኬፕቨርዴን ማሸነፍ ይጠበቅባታል።