በስልጤ ዞን በቤተክርስቲያናት እና በቤተአምልኮዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ጉባኤው አወገዘ
“ወንጀልን በሌላ ወንጀል ለማረም መሞከር ሕገ ወጥነት ነው” ብሏል ጉባኤው
መንግስት ሕግና ስርአትን ለማስፈፀም ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ህጎችን ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ብሏል የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት ቤተ አምልኮዎች ላይ ተፈጽሟል ያለውን የወንጅል ድርጊት አውግዟል፡፡
ጉባኤው ወንጀልን በሌላ ወንጀል ለማረም መሞከር ሕገ ወጥነት ብሏል፡፡
ተግባሩ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ደረቅ ወንጀልና በህግ ሊያስጠይቅ የሚገባው ተግባር ነው ብሎ በጽኑ ያምናልም ብሏል ጉባኤው፡፡
ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተፈፀመወን አስነዋሪ ተግባርን አስመልክቶ ተግባሩን የሚያወግዝ መግለጫ መውጣቱን ያስታወሰው ጉበኤው፤ ትናንት በወራቤ በሆነው እጅጉን እንዳዘነም ገልጿል፡፡
“ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚሰብኩ፣ ትህትናን የሚስተምሩና ለሌሎች ስለመኖርና መስዋዕት ስለመክፈል የሚገዳቸው እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በሃይማኖት ስምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀመው ሁሉ ሕገ ወጥና ደረቅ ወንጀል እንደሆነ ታውቆ መንግስት ሕግና ስርኣትን እንዲያስጠበቅ ጉባኤያችን አበክሮ ይጠይቃል”ም ብለዋል ጉባኤው፡፡
መንግስት ሕግና ስርአትን ለማስፈፀም እንዲችል ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ህጎችን ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባል ሲልም አክሏል፡፡
ጉባኤው፤ ሕዝበ ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ ክርስቲያኑ በየትኛውም አካባቢ የተከሰተው ችግርና የደረሰው ውድመት ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው መሆኑ በመገንዘብ፤ አካባቢያቸውን በጋራ በመጠበቅ፣ ችግሮች እንዳይባባሱም አንዱ ሌላውን በመጠበቅ የበኩላችሁን ሃላፊነት እንዲወጣ ሲልም አሳስቧል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲደያው መልዕክት የሚላላኩ አካላት በሚጽፉት ጽሁፍና በሚያስተላልፉት መልዕክት ሀገራቸውንና ወገናቸውን ጉዳት እንዳይጋለጥ ሁሉንም ተግባር በማስተዋል ሊያከናውኑ እንደሚገባም ጠይቋል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ የሀድያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ባወጣው መግለጫ የወራቤ ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያ “በአክራሪ ኃይሎች” በእሳት መውደሙን እና በውስጡ ያሉቴ ንዋየ ቅዱሳት መቃጣላቸውን አስታውቋል፡፡
የተጎዱ ክርስቲያኖች ህክምና እንዲደረግላቸው እና በዞኑ በጫና ስር ያሉት አበያተክርስቲያናት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቀው ሀገረስከቱ፤ ውድመት ሲደርስ የዞኑ የጸጥታ ኃይል አለማስቆሙ እንዳሳዘነው ሀገረ ስብከቱ ገልጿል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭትን ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማስፋፋት የሚደረግ እንቅስቃሴን እንደማይታገስ እና ርምጃዎችንም እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ግጭቱን አጸያፊ በሆነ መልኩ ወደ ወራቤ አካባቢ ለማስፋፋት የሚካሄደው የተናበበ የሚመስል እንቅስቃሴ የእስልምናም የክርስትናም አማኞች እንቅስቃሴን እንደማይወክል የአገልሎቱ ሚኒስቴር ለገሰ ቱሉ ተናግረዋል፡፡