በጎንደር ከተማ የተቀሰቀውን ግጭት በመቆጣጠር አካባቢውን ለማረጋጋት መቻሉን የአማራ ክልል ገለጸ
ጥፋተኛ በሆኑ አካላት ላይ አስፈላጊውን ኹሉ እርምጃ እንደሚወስድም ነው የገለጸው
ግጭቱ የሕዝቡን አንድነት ለመስበር በማሰብ የተቀሰቀሰ ነው ያለው ክልሉ የህይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል
ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ በጎንደር ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ጥፋተኛ በሆኑ አካላት ላይ አስፈላጊውን ኹሉ ሕጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም እንደሚወስድ የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ፡፡
ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ/ም አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተቀሰቀሰው ብጥብጥ የህይወት እና የአካል ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግስቱ ግጭቱ የሕዝቡን አንድነት ለመስበር በማሰብ የተቀሰቀሰ ነው ያለው የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ እንደ አባት ይታዩ በነበሩት በታላቁ ሸኽ ከማል ለጋስ ሥርዐተ ቀብር ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጸብ ግጭቱ መቀስቀሱንም ነው ክልሉ ያስታወቀው፡፡
ለቀብር ስነ ስርዓቱ የሚሆን ድንጋይ ድንበርተኛ ከኾነ ቤተ ክርስቲያን ላይ "እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው" በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ጸብ ነው ግጭት የተቀሰቀሰው፡፡
በግጭቱም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል እንደ ክልሉ መንግስት መግለጫ።
በመግለጫው በማንኛውንም አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ኾነ በንጹሐን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋትን የሚሸከምበት ጫንቃ እንደሌለው የገለጸም ሲሆን በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን ኹሉ ሕጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ግጭቱን ለማብረድ፤ በድርጊቱ የተሳተፉትንና ግጭቱን እያባባሱ ያሉ አካላትንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።
በዚህም አካባቢውን በማረጋጋት እና ሕግና ሥርዐትን በማስከበር ግጭቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መቻሉንም ገልጿል፡፡
የወንጀሉን ተጠርጣሪዎች በሕግ ጥላ ሥር የማዋል፣ ተጎጅዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው የማጣራት ሥራዎችን በማከናወን በይህወትና በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለሕዝብ አሳውቃለሁም ብሏል የክልሉ መንግስት፡፡
የከተማው ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን እንዲተባበርም ጠይቋል፡፡
ግጭቱን ተከትሎ በተከሰተው ብጥብጥ የሁለቱንም ሃይማኖት ተከታዮች የማይወክል ጥፋት ተፈጽሟል ሲል መግለጫ ያወጣው የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት በበኩሉ የህይወት እና የአካል ጉዳት ያደረሱ እንዲሁም በዘረፋ ተሰማርተው የነበሩ አካላት እየተያዙ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ በብጥብጡ ለግጭት በማያበቁ ምክንያቶች ጎንደርን የማቃጠል፣ የመዝረፍና የማዋረድ ተልዕኮ በነበራቸው አካላት በተቀነባበረና በተመራ ሴራ መቀስቀሱን የገለጸም ሲሆን በፀጥታ መዋቅሩ፣ በሃይማት አባቶችና ወጣቶች እንዲሁም በሃገር ሽማግሌዎች ጥረት የተፈለገው ጥፋት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቋል፡፡
በተፈጠረው ችግር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የተገኙ ሙስሊሞች እንደ ነበሩና የእምነቱ አባቶችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ለፀጥታ አካላት ያስረከቡ መሆኑን በተመሳሳይም በመስጊድ ውስጥ የተጠለሉ የክርስትና አማኞች እንደነበሩም ነው የገለጸው፡፡
በህይዎትና በአካል ጉዳት እንዲሁም በዘረፋ የተሰማሩት አጥፊዎች እየተለቀሙና እየተያዙ መሆኑም በመግለጫው አስቀምጧል፡፡