የጨረቃ ምልከታን መሰረት ያደረገው የሲዳማ ዘመን መለወጫ “ፊቼ ጨምባላላ” ተከበረ
በበዓሉ ላይ በሺዎች የሚቆጥር ህዝብ ታድሟል
የሲዳማ ክልል በ2012ዓ.ም በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ 10ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ መዋቀሩ ይታወሳል
የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለዋጫ በዓል ፍቼ ጨምባላላ በሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ተከብሯል፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ በመከበር ላይ ባለው የፍቼ ጨምባላላ በዓል ላይ የሲዳማ እና የኦሮሚያ ክልሎች ፕሬዝደንቶችን ጨምሮ ሚኒስትሮች እና የክልሉ ባለስልጣናት ታድመዋል፡፡ በበዓሉ ላይ በሺዎች የሚቆጥር ህዝብ በአንድ ቦታ በመሰባሰብ አክብሮታል፡፡
በዓሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ አኩሪ በዓል ነው ያሉት የሲዳማ ክልል ፕሬዝደንት ደስታ ሌዳሞ፤ በዓሉ አብሮነት እና ተባብሮ ማደግን የሚያስተምር እሴት አለው ብለዋል፡፡
“እኛ ሲዳማች በዚህ እሴት ተኮትኩተን በማደፈጋችን፤ በተለያያ ጊዜ በዚህ አካባቢ መተባበር እና መረዳዳት መገለጫችን ሆኖ” መዝለቁን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላም ቢሆን በውስጡ ያሉት ብሄሮች በፍቅር መያዙን እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር የሆኑት ቀጀላ መርዳሳ በኩላቸው ሲዳማዎች የጨረቃ ምልከታን በመመርኮዝ የራሳቸውን የቀን መቁጠሪያ ስሌት መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
“ሲዳማዎች ልዩ የሚያደርጋቸው የወር እና የአመት አቆጣጠራቸውን በመከታተል የዘመን መለወጫ በዓል መቼ እንዲሚሆን ተለይቶ የሚታወቅበትን በክዋክብት ምልከታ ላይ የተመሰረተ ባህላዊ የቀን መቁጠሪያ ስሌት ቀምረው ለአገልግሎት” ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ፤የጨምባላላ በዓልን በማልማትና በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የቱሪዝም ምንጭ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በሲዳማን ዞን በኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ መሰረት፤ የሲዳማ ዞን የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል ሆኖ ጸድቋል፡፡ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔም ሲዳም ክልል ይሁን የሚለው ድምጽ 98.51 በመቶ እንደነበር ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አስታውቋል፡፡