ለግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ አዲስ ሀገር አቀፍ የቴሌኮም ፈቃድ እንዲሰጥ ተወሰነ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታሪካዊ ውሳኔ ወስኗል” ብለዋል
ኩባንያው በአጠቃላይ ከ8 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ሙዓለ ነዋይ እንደሚያፈስ ጠ/ሚ ዐቢይ ገልጸዋል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 96ኛ መደበኛ ስብሰባ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለውጭ ኦፕሬተሮች ስለመስጠት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከፍተኛ የፈቃድ ክፍያ ዋጋ እና አስተማማኝ የሙዓለ ነዋይ ፍሰት ዕቅድ ላቀረበው ለግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ፣ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን አዲስ ሀገር አቀፍ የቴሌኮም ፈቃድ እንዲሰጥ በአንድ ድምፅ አጽድቋል” ብለዋል። በዚህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ታሪካዊ ውሳኔ” መወሰኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ከ 8 ቢሊዮን ዶላር በሚበልጥ የሙዓለ ነዋይ ፍሰት፣ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ከተደረጉት የውጪ ቀጥተኛ የሙዓለ ነዋይ ፍሰቶች የአሁኑ ኩባንያ ብልጫ እንዲኖረው እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል አገልግሎት የማስገባት “ዕቅዳችን ፈር ይዟል” ሲሉም ነው ጠ/ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያስታወቁት።
ግልጽነት እና ውጤታማነት የሞላበት ያሉትን ይህን ሂደት ላሳኩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመቅረጽ ሲተገብራቸው ከነበሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዳዮች መካከል በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ ስራዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ አንዱ በቴሌኮም አገልግሎት ልምድና አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ለማስቻል ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ሲሰራ የነበረው ስራ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ከአንድ ዓመት በፊት ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ለቀረበው ጥሪ የጨረታ ሰነዱን ከገዙ ዘጠኝ ድርጅቶች መካከል ሁለት ኩባንያዎች መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህም፡
1. ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ (Global partnership for Ethiopia)-Vodafone, Vodacom, Safaricom, Sumitomo Corporation, and the CDC Group የተባሉ ዓለምአቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በጥምረት ያቋቋሙት ኩባንያ እና
2. ኤምቲኤን-MTN International (Mauritius) Limited የተሰኙ ኩባንያዎች የጨረታውን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በተራ ቁጥር 1 የተጠቀሰው ድርጅት የኦፕሬሽን ፈቃድ ለማግኘት ያቀረበው ዋጋ 850 ሚሊየን ዶላር (2ኛው ድርጅት ካቀረበው ዋጋ በ250 ሚሊየን ዶላር ብልጫ አለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፡፡ በመሆኑ፤ ለ 1.5 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ፤ ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት በሀገር ውስጥ የሚያከናውን በመሆኑ ለግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ ፈቃድ እንዲሰጥ መወሰኑን ነው ጽ/ቤቱ የገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን በኩል ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑም በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት መግለጫ ተጠቅሷል፡፡