የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል የህግ አውጪ እና አስፈጻሚ አካላት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግ አስታወቀ
የትግራይ መንግስት በበኩሉ ከመስከረም 25 በኋላ ህጋዊ ስልጣን ያለው የፌዴራል መንግስት እንዳማይኖር ማስታወቁ የሚታወስ ነው
ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉም ተገልጿል
የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል የህግ አውጪ እና አስፈጻሚ አካላት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግ አስታወቀ
በህገወጥ መንገድ የተቋቋመ ነው ላለው የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ካቢኔ የፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ እንደማያደርግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት እና ከፍተኛው የህግ አስፈፃሚ አካል (ካቢኔ) ህገመንግስታዊ ቅቡልነት የላቸውም ያለው ምክር ቤቱ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉ ገልጿል፡፡
ተቋማቱ የክልሉን ከፍተኛ ስራ አስፈፃሚ አካላት እንደ ህጋዊ አካል በመቁጠር ደብዳቤ መፃፃፍ፣ መረጃ መላላክ፣ ድጋፎች ማድረግ፣ በፌዴራል ደረጃ በሚካሄዱ መድረኮች ላይ ማሳተፍ እንደማይችሉም ነው የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ የተናገሩት፡፡
በአንጻሩ የክልሉ ህዝብ መሰረታዊ የልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚነቱ እንዳይስተጓጎል እንደ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ከተማ ካሉ ህጋዊ የክልሉ መዋቅሮች ጋር ብቻ ግንኙነት እንደሚደረግ እና ይህም በሚዋቀር ኮሚቴ ክትትል እንደሚደረግ አፈ-ጉባዔው በተለይ ለኢቲቪ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ሊደረስ የቻለው የትግራይ ክልል መንግስትና ገዥው ፓርቲ ህውሃት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ባከበረ መልኩ የስራ ዘመኑ በምክር ቤቱ ውሳኔ የተራዘመውን የክልሉን ምክር ቤት የህግ አስፈፃሚ አካል ወደ ቦታው መመለስ ስላልቻሉ ነው ብለዋል አፈ ጉባኤው፡፡
ውሳኔው የትግራይ ህዝብ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ እየተከተለ ባለ ቡድን ምክንያት ከሰላም፣ልማትና መሰረታዊ አገልግሎት አንፃር እንዳይጎዳና የትግራይ ህዝብ እንደሌሎች የአገራችን ህዝቦች መሰረታዊ የልማትና የደህንነት አገልግሎቶች እንዲያገኙ ታስቦ መተላለፉንም አመልክተዋል፡፡
‹‹ይሄ ሊሆን የቻለው ለትግራይ ህዝብ ካለን ክብር ነው›› ያሉት አቶ አደም ‹‹ ህዝብም እንደ ሌሎች የአገራችን ህዝቦች ሊያገኘው የሚገባውን ጥቅም ሊከበርለት ይገባል ከሚል ጽኑ እምነት የመነጨ ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የውሳኔ አፈፃፀምም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል፡፡
በቀጣይ በክልሉ ካሉ የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በተለይ ህዝቡ ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝ በጥናት ተመስርቶ ተፈፃሚ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት የ6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ መራዘም በመቃወም የራሱን ክልላዊ ምርጫ ያደረገው የትግራይ ክልል ህገ መንግስቱን በብቸኝነት እንዳከበረ በመግለጽ ከመስከረም 25 በኋላ የፌዴራሉ መንግስት ህጋዊ የስልጣን ዘመን እንደሚያበቃ እና እውቅና የሚሰጠው የፌዴራል መንግስት እንደማይኖር ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ይህ የድጎማ በጀቱን የተመለከተው ውሳኔ በፌዴራሉ እና በክልሉ መንግስት መካከል ያለውን ውጥረት ይበልጥ እንደሚያከረው ይጠበቃል፡፡