ም/ቤቱ የአውሮፓ ህብረት ከታዛቢነት የወጣበት ምክንያት ግልጽ እንዲደረግለት ጠየቀ
ም/ቤቱ መንግስትና ህብረቱ ጉዳዩን ግልጽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጿል
ም/ቤቱ ጉዳዩን በተመለከተ “መንግስትም፣ ህብረቱም ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ወይም ሪፖርት ሊሰጡን ይገባል”ብሏል
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ዛሬ በሰጠው መግለጫ የአውሮፓ ህብረት ለምርጫ 2013 ታዛቢ የመላክ እቅዱን የሰረዘበትን ምክንያት እንደማያውቅ አስታወቀ፡፡
ም/ቤቱ መንግስትና ህብረቱ ጉዳዩን ግልጽ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
የምክር ቤቱ ስብሳቢ ዶ/ር ራሔል ባፌ በመግለጫቸው ህብረቱ ምርጫውን ላለመታዘብ የወሰነበት “ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ አልተቀመጠም፤መንግስት ያሳወቀን ነገርም የለም” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ራሔል ባፌ ጉዳዩን “መንግስትም፣ ህብረቱም ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ወይም ሪፖርት ሊሰጡን ይገባል” ብለዋል፡፡
ሰብሳቢዋ እንደገለጹት የኢትዮጵያ መንግስት ህብረቱ ሉአላዊነትን የሚዳፈር ስራ ውስጥ ተንቀሳቅሷል ስለማለቱ ቢሰሙም ስለሂደሉ ግን “አናውቅም” ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሰብሳቢዋ ህብረቱ የመታዘብ እቅዱን የሰረዘበትን ምክንያት እንዲብራራ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫው ባለድርሻ አካል በመሆናቸው ህብረቱ ውሳኔውን ሊያሳውቃቸው እንደሚገባ ሰብሳቢዋ ዶ/ር ራሄል ባፌ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነውና ኢትጵያን ሉአላዊነት በማይዳፈር መልኩ ምርጫውን እንዲታዘብ ም/ቤቱ ጠይቋል፡፡
በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት "ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አልተሟሉም" በማለት ለምርጫ 2013 ታዛቢ የመላክ እቅዱን መሰረዙን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ህብረት በምርጫው ጉዳይ እንደማይታዘብ ያስታወቀው፣” የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ስራ ልስራ ብሎ ስላልተፈቀደለት” ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ዲና እንደገለጹት ህብረቱ ምርጫ ሲታዘብ መጠቀም በሚፈልገው የመረጃ ቴክኖሎጂ እና የምርጫ ውጤት ከምርጫ ቦርድ ቀድሜ ይፋ ላድርግ የሚሉት ፋላጎቶቹ “የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ስለሚፈታተን” ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡