የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጀብሃ ጀምሮ የባዕድ ተጽዕኖ ነበረባቸው ተባለ
ከ1953 እስከ 1983 የነበሩት የኢትዮጵያ ፓርቲዎች “በሴራ የተካኑ” ነበሩ ብለዋል ጥናት አቅራቢው
የብልጽግና ፓርቲ አመራር አለሙ ስሜ ከ1983 በፊት የነበሩት ፓርቲዎች ከነችግራቸው ያላማ ጽናት ነበራቸው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል
የብልጽግና ፓርቲ አመራር አለሙ ስሜ ከ1983 በፊት የነበሩት ፓርቲዎች ከነችግራቸው ያላማ ጽናት ነበራቸው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል
ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዘጋጅነት በተካሄደ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት እና ችግሮች ላይ ጥናታዊ ጹሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
በዚህ ጥናታዊ ጹሑፍ ላይ በኢትዮጵያ የፓርቲዎች አመሰራረትና መዋቅር እንዲሁም የነበሩ ጥንካሬዎችና ችግሮች ላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡
የዚህ ጥናት አቅራቢና የራያ ራዩማ ፓርቲ አመራር አቶ አግዘው ሕዳሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተጽዕኖ ነጻ እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም በግብጽ ለትምህርት የተላኩ ወጣቶች ጀብሃን መመስረታቸውን በማንሳት፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ 1953 እስከ 1983 በሚለው ጹሑፋቸው ላይ እንደገለጹት በነዚህ ጊዜያት የነበሩ ፓርቲዎች ውስጥ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ ነበሩም ብለዋል፡፡ መጠላለፍና መገፋፋት የበዛበት ጊዜ እንደነበር ያነሱት አቶ አግደው፤ የውጭ ሀገራት ተጽዕኖም ቀላል እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ አመራር ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው ከ1983 በፊት ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ለዓላማቸው ያላቸው ጽናት ግን የሚደነቅ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ከ1983 በኋላም ቢሆን በፓርቲዎች ውስት ችግሮች እንደነበሩ ጹሑፍ አቅራቢው ገልጸዋል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የጠራና ግልጽ የሆነ ፕሮግራም ይዞ በመቅረብ ደረጃ ችግር እንዳለባቸው አቶ አግዘው አንስተዋል፡፡
በተለይም ከ1983 በኋላ ብቃት ያላቸው ሰዎች ከፖለቲካው እየተገለሉ ደካሞችና ብቃት የሌላቸው ወደ ፖለቲካው መድረክ ሲመጡ እንደነበር በጹሑፋቸው አስፍረዋል፡፡
በዚህ ምክንያትም በድህነት ውስጥ እየማቀቀ ያለው ሕዝብ ወደ ከፋና ወደባሰ ምስቅልቅል እንዲገባ እየተደረገ ነው ሲሉም ያነሳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ፓርቲዎች በብሔርና በጎሳ ከመደራጀት ባለፈ በአጀንዳዎች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በጥቅሉ ፓርቲዎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በማገናዘብ መሆን እንዳበት ገልጸዋል፡፡