ፖለቲካ ፓርቲዎች ከነገ ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃን የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ ይጀምራሉ
ፓርቲዎቹ ከመጋቢት 30 እስከ ግንቦት 23 ነፃ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በብዙኃን መገናኛዎች ማድረግ እንደሚችሉም ነው የተገለጸው
![](https://cdn.al-ain.com/images/2021/4/07/244-140845-frg_1606d84ad96ffe_700x400.jpg)
ለምርጫ ቅስቀሳው በሬዲዮ 620፣ በቴሌቪዥን 425 ሰዓት እንዲሁም በጋዜጣ 615 አምድ ተመድቧል
በ6ኛው ሃገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከነገ ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ አምድ እጣ ድልድል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ብሮድካስት ባለሥልጣን በተዘጋጀ የጋራ መድረክ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
በድልድሉ መሰረት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅሰቀሳ በሬዲዮ 620 ሰዓታት፣ በቴሌቪዥን 425 እንዲሁም በጋዜጣ 615 አምድ ተደልድሏል።
ድልድሉ ፓርቲዎች ለፌደራል እና ለክልል ምክር ቤቶች ባቀረቡት እጩ ብዛት እንዲሁም ባስመዘገቡት የሴቶች እና የአካል ጉዳተኛ እጩዎች ብዛት የተሰራ ነው፡፡
በዚህም 25 በመቶ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሚከፋፈል ሲሆን 40 በመቶ ባቀረቡት የእጩዎች ብዛት የሚደለደል ይሆናል።
እንዲሁም ለሴት እጩዎች 20 በመቶ፣ ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ 10 በመቶ ይደለደላል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ አሸንፈው ወደ ምክር ቤት የገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በነበራቸው የመቀመጫ ብዛት ልክ የ5 በመቶ ድርሻ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
በእያንዳንዱ ሚዲያ የተመደበ ሰዓት የመንግስት ሬዲዮ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ 30፣ 30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ የሚጠቀሙበት እንደሆነ ተገልጿል።
የመንግስት ወይም የህዝብ ቴሌቪዥን የሚባሉት ኢቲቪ፣ ኦቢኤን፣ አማራ ቲቪ፣ ደቡብና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከሰኞ እስከ አርብ ቀንና ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 300 ደቂቃ አገልግሎቱን ይሰጣሉ።
ሌሎች የክልል ሚዲያዎች ደግሞ ከሰኞ እስከ አርብ ዘወትር ማታ ማታ 30 ደቂቃ በሳምንት 150 ደቂቃ፤ የንግድ ቴሌቪዠን በሳምንት 2 ቀን ዘወትር ማታ ማታ ለ30 ደቂቃ በሳምንት 60 ደቂቃ ያገለግላሉ።
ድልድሉ በ60 ሚዲያዎች ላይ የተደረገ ነው፡፡
ፓርቲዎች በተደለደለላቸው እጣ መሠረት ከመጋቢት 30 እስከ ግንቦት 23 በመገናኛ ብዙኃን ነፃ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።