“2024 YR4” የጠፈር አለት ሊወድቅባቸው የሚችሉ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የአንድ ስታዲየም ስፋት ያለው አለቱ ምድርን የመምታ እድሉ 2 በመቶ ሲሆን፤ በ2032 መሬት ላይ ይደርሳል

ተመራማሪዎች ሊመቱ ይችላሉ በሚል ከዘረዘሯቸው ሀገራት ውስጥ ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ናይጄሪያ ተካተዋል
የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች “አስትሮይድ 2024 YR4” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን እና በፈረንጆቹ በ2032 ምድር ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላ የተባለውን የጠፈር አለት እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከ40 እስከ 100 ሜትር ስፋት ሊኖረው ይችላል የተባለው “2024 YR4” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የጠፈር አለት ምድርን የምታ እድሉ 2 ከመቶ ብቻ ነው የተባለ ሲሆን፤ ምድር ላይ ጉዳት ሳደርስ የማለፍ እድሉ ግን 98 በመቶ እንደሆነም ተነግሯል።
የአንድ ስታዲየም ስፋት መጠን አለው የተባለው ይህ የጠፈር አለት በመጠኑ ባለፉት ስምንት ዓመታት ወደ ምድር ከመጡት ውስጥ ትልቁ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ጠፈር ሳይንስ ምርምር ማዕከል ወይም ናሳ እንደገለጸው ከሆነ አሜሪካ በዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓኗ ሂሮሽማ ላይ ከጣለችው ቦምብ በመቶዎች እጥፍ ሀይል ያለው የጠፈር አለት ወይም አስተሮይድ ወደ ምድር እየመጣ ነው ብሏል፡፡
የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች “አስትሮይድ 2024 YR4” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የጠፈር አለት ከእይታ ከመሰወሩ በፊት እቅስቀሴውን እየተከታተሉት ነው ተብሏል።
የጠፈር አለቱ አንድ ጊዜ ከእይታ ከተሰወረ መልሶ ለማግኘት እና ለመመልከት እስከ 2028 መጠበቅ የግድ እንደሚልም ተነግሯል።
“2024 YR4” ሊወድቅባቸው የሚችሉ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
እንደተገመተው ከሆነ እና ምድርን የመምታ የ2 በመቶ እድሉ እውን ከሆነ አፍሪካ፣ ፓስፊክ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ይህ ጠፈር አለት ያርፍበታል ተብሎ ከሚጠበቁ ቦታዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በእነዚህ አህጉራት ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት መካከል የበለጠ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ሀገራትም ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ ኮሎምቢያ እና ኢኳዶር እንደሚገኙበት ተነግሯል።
ዓለም አቀፉ የጠፈር አለት ማስጠንቀቂያ ማዕከል፤ ወደ ምድር እየመጣ ያለውን የጠፈር አለት ወይም አስተሮይድ ጉዳት ለመቀነስ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አሁን ላይ ወደ ምድር እየመጣ ነው የተባለው ይህ ግዙፍ ዓለት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ካይነቲክ ኢመፓክተር የተሰኘ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጉዳት ወደማያደርስ መልኩ መቀየር እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ይሁንና ይህንን ቴክኖሎጂ ለመተግበር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የበለጸጉ ሀገራት ወጪውን የሚሸፍኑት በአለቱ ሊጠቁ እንደሚችሉ ከተገነዘቡ ብቻ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡