በሩሲያ ኤሮስፔስ ኃይል የጠፈር ተዋጊዎች “ኮስሞስ-2560” መንኮራኩርን በተሳካ ሁኔታ ስራ አስጀምረዋል
ሩሲያ አዲስ ወታደራዊ ሳተላይት ወደ ጠፈር ማስወንጨፏ ተነግሯል።
ከሰባት ወር በፊት የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ሀያላን ሀገራት ጎራ ለይተው ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ።
ይህንን በተመለከት አስተያየት የሰጡት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሼጉ፤ ሀገራቸው በዩክሬን እያደረገች ባለው ጦርነት በተዘዋዋሪ ከምእራባውያን ጋር ውጊያ ላይ መሆኗን መናገራቸው ይታወሳል።
ሚንስትሩ ከ200 በላይ የሲቪል ሳተላይቶች ለዩክሬን ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ተናግረው ነበር።
ሩሲያ ይህንን በሳተላይት በመታዝ የእየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመመከት ያስችላታል የተባለ አዲስ የጦር ሳተላይት በባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት ወደ ጠፈር አምጥቃለች።
“ኮስሞስ-2560” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ወታደራዊ ሳተላይት አርካንግልስክ ክልል ከሚገኘው ከፕሌሴስክ ወታደራዊ መንደር ማስወንጨፏን አር.ቲ ዘግቧል።
ሩሲያ ያስወነጨፈችው አዲሱ ወታደራዊ ሳተላይት ኦርቢት ላይ ደርሶ ምድር ላይ ካለ የመቆጣጠሪ ጣቢያ ጋር ግንኙት ማድረጉን እና በአግባቡ ስራ መጀመሩ ተነግሯል።
ሳተላይቱን በሩሲያ ኤሮስፔስ ኃይል ውስጥ የጠፈር ተዋጊዎች ያስወነጨፉት ሲሆን፤ ተዋጊ ሃይሎቹ ሳተላይቱን አግራ 1.2 በተባለ ዘመናዊ ማስወንጨፊያ ተሸከርካሪ በመጠቀም የተሳካ ስራ መስራታቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።