እስራኤል በጋዛ በምታደርገው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሀገራት አምባሳደሮቻቸውን በመጥራት በእስራኤል ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል
በጦርነቱ ምክንያት ከእስራኤል አምባሳደሮቻቸውን የጠሩ ሀገራት እነማን ናቸው?
እስራኤል በጋዛ በምታደርገው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሀገራት አምባሳደሮቻቸውን በመጥራት በእስራኤል ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ሀማስ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ያልተጠበቀ እና ከባድ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል የሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ ላይ የማያባራ ጥቃት እያደረሰች ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የሰብአዊ ሁኔታው ያሳሰባቸው ቢያንስ ስምንት የሚሆኑ ሀገራት በእስራኤል የነበሯቸውን አምባሳደሮች መጥራታቸውን አለፍአቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ያለው መጠነሰፊ ጥቃት እንደአሜሪካ ባሉ አጋሮቿ ሁለንተናዊ ድጋፍ ቢቸረውም፣ የአረብ ሀገራትን ጨምሮ በርካቶች ተኩስ እንድታቆም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
ብዙ የአለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በቀጣናው የሰብአዊ ቀውስ ያስከትላል ሲሉ አስተጠንቅቀዋል።
ይህን በመቃውም ስምንት ሀገራት አምባሳደሮቻቸውን ከእስራኤል ጠርተዋል።
የደቡብ አሜሪካዋ ቦልቪያ አምባሳደሯን በማስወጣት የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።
አምባሳደሮቻቸውን ያስወጡ ሀገራት የሚከተሉት ናቸው።፦
ደቡብ አፍሪካ
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለፈው ሰኞ እለት አምባሳደሩን በማስወጣት በእስራኤል የነበረውን የዲፕሎማሲ ተልእኮ አቋርጧል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ሚኒስትር ኩምቡድዞ ንሻቨህኒ ደቡብ አፍሪካ አምባሳደሯን ለማስወጣት የወሰነችው እስራኤል አለምአቀፍ የሰብአዊ ህግ አለማክበሯ አበሳጭቷት ነው ብለዋል።
ጆርዳን
ጆርዳን 10ሺ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት የሆነውን ጦርነት በመቃወም ባለፈው ሳምንት አምባሳደሯን አስወጥታለች።
ጆርዳን በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ አጋር ስትሆን የፍልስጤም ስደተኞችን ለዘመናት የምታስተናግድ ሀገር ነች።
የጆርዳን መንግስት አምባሳደሩን ያስወጣው ያልተጠበቀ የሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር እና ንጹሃን እንዲገዱ ምክንያት የሆነውን ጦርነት ለመቃውም እና ለማውገዝ እንደሆነ ገልጿል።
ቱርክ
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን እስራኤል የአለምአቀፍ ህጎችን በመጣስ፣ ንጹሃንን በመግደል በሂደት ፍልስጤማውያንን ከታሪክ ለማጥፋት እሰራች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ቱርክ ባለፈው ቅዳሜ አምባሳደሯን አስወጥታለች።በቱርክ ኤርዶጋን የተገኙበት ጸረ-እስራኤል የሆነ ህዝባዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።
ቺሊ
የእስራኤልን የጋዛ ጥቃት ያወገዙት የችሊው ፕሬዝደንት ገብሬል ቦሪክ ባለፈው ሳምንት ነበር ቺሊ አምባሳደሯን እንደምታስወጣ ያስታወቁት። የቺሊ መንግስት እስራኤል አለምአቀፍ ህግን በመጣስ "ፍልስጤማውያንን በጅምላ እየቀጣች ነው" ብሏል።
ኮሎምቢያ
ኮሎምቢያ በጋዛ እየደረሰ ያለውን የንጹሃን ግድያ በመቃወም አምባሳደሯን ከእስራኤል ባለፈው ሳምንት አስወጥታለች። የኮሎምቢያ መንግስት ባወጣው መግለጫ ቺሊ እስራኤል አለምአቀፍ ህግን እንድታከብር እና ተኩስ እንዲቆም ጠይቃለች።
ቻድ
አፍራካዊቷ ቻድም አምባሳደሯን አስወጥታለች የሚሉ በርካታ ዘገባዎች ወጥተዋል። የቻድ መንግስት በጦርነቱ በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ አውግዟል።
ሆንዱራስ
የሆንዱራስ ፕሬዝደንት ጦማራ ካስትሮ በኤክስ ወይም ቀደም ሲል ትዊተር በሚባለው ገጻቸው እስራኤል ያሉትን አምባሳደር መጥራታቸውን አስታውቀዋል። ካስትሮ እንደገለጹት አምባሳደሪ የተጠሩት በፍልስጤማውያን ላይ ከባድ የሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ነው።
ባህሬን
የባህሬን ፖርላማ በእስራኤል የባህሬን አምባሳደር መመለሳቸውን አስታውቋል። ፖርላማው በባህሬን የእስራኤል አምባሳደርም ወደሀገራቸውን መሄዳቸው ጠቅሷል።